Horn Insight

Horn Insight

Share

Photos from Horn Insight's post 10/07/2026

የቀድሞ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር አለሙ ጣሚሶ ተከሰሱ

ዶ/ር አለሙ ጣሚሶ የቀረበባቸውን ክስ "መሠረተ ቢስ ማጥላላት ነው" ሲሉ አስተባብለዋል

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ውስጥ የፌዴራል መንግስትን የፋይናንስ መመሪያዎችንና አሰራሮችን በመተላለፍ ከፍተኛ የሕግ ጥሰት ፈጽመዋል በተባሉ የቀድሞ የኮሌጁ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ላይ ጥብቅ የዲሲፕሊን እርምጃ እንዲወሰድ በይፋ መጠየቁ ታውቋል።

የኮሌጁ አስተዳደር ጉዳዩን መርምሮ የሕግ ጥሰቶቹን ለይቶ በማደራጀት፣ በአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት በኩል ለዋናው ግቢ የአካዳሚክ ዲሲፕሊን ኮሚቴ መምራቱን ይፋዊ ደብዳቤዎች ያመለክታሉ።

ይሁን እንጂ የክሱ ዋና ኢላማ የሆኑት የቀድሞው ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር አለሙ ጣሚሶ የቀረበባቸውን ውንጀላ "እርስ በርሱ የሚጋጭና መሠረተ ቢስ ማጥላላት ነው" ሲሉ በጽኑ ተቃውመዋል።

ይህ የእርምጃ ጥያቄ የቀረበው የዩኒቨርሲቲው የውስጥ ኦዲት ሥራ አስፈጻሚ ከመጋቢት 01/2016 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 30/2017 ዓ.ም ባሉት ስምንት ወራት ውስጥ ባደረገው የሂሳብ፣ የንብረት እና የሥራ ላይ ትምህርት ፈቃድ አሰጣጥ ምርመራ ሪፖርት ላይ ተመስርቶ ነው። በዚሁ የኦዲት ግኝት መሠረት፣ የኮሌጁ የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር እንዲሁም ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር በነበሩት ዶ/ር አለሙ ጣሚሶ አመራር ወቅት መጠነ-ሰፊ የፋይናንስና የአስተዳደር ግድፈቶች መፈጸማቸው በዝርዝር ተመልክቷል። ከተገኙት ዋና ዋና የሕግ ጥሰቶች መካከል ክፍያዎች በቀጥታ ለባለ መብቶቹ መከፈል ሲገባቸው በተለያዩ የሂሳብ ሠራተኞች ግል አካውንት ውስጥ ገቢና ወጪ እንዲሆን መደረጉ፣ ያለ ነዳጅ መጠየቂያ ቅጽና ያለ ባለሙያ ፊርማ ክፍያዎች መፈጸማቸው፣ እና የአየር ጉዞ ቲኬቶች ያለ ቦርዲንግ ፓስ (Boarding Pass) መከፈላቸው ይገኙበታል።

በንብረት አስተዳደር በኩልም ሳምሰንግ ሞባይል ስልክን ወደ ካሜራ ቀይሮ መጻፍ፣ በአንድ ግለሰብ ስም በአንድ ጊዜ እስከ 15 ታብሌት ኮምፒውተሮችን ወጪ አድርጎ መገኘት የመሳሰሉ ግኝቶች የተመዘገቡ ሲሆን፣ ዶ/ር አለሙን ጨምሮ 15 የሚሆኑ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ሕጋዊ የትምህርት ውል ሳይገቡ ለሦስተኛ ዲግሪ (PhD) ሲማሩ መቆየታቸው ተገልጿል። በዚህም ምክንያት ኮሌጁን በአግባቡ ባለመምራታቸው ከአመት በፊት ዶ/ር አለሙ ጣሚሶ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ የተደረገ ሲሆን፣ ዩኒቨርሲቲው ለትምህርት ማስረጃቸው እውቅና እንዳልሰጠ እና “ዶክተር” የሚለውን የማዕረግ ስም መጠቀም እንደማይችሉ በጽሑፍ ገልጾላቸዋል።

በተቃራኒው የቀድሞው ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር አለሙ ጣሚሶ 03 /10/2018 ዓ.ም በጻፉት ይፋዊ የቅሬታና የማብራሪያ ጠያቂ ደብዳቤ፣ የቀረበባቸው ክስ ሕጋዊ መሠረት የሌለው እና በተቋሙ ውስጥ ለ8 ዓመታት በታማኝነት ባበረከቱት አገልግሎት ላይ ያነጣጠረ የማጥላላትና የማሳደድ ዘመቻ አካል ነው ሲሉ ውድቅ አድርገውታል። በኦዲት ሪፖርቱ ላይ የተመሠረተው ክስ እርስ በርሱ የሚጋጭ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር አለሙ፣ በአንድ በኩል ክፍያዎችን ያለአግባብ በመፍቀድ ተጠያቂ ሲያደርጋቸው፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሕጋዊ የማጽደቅ ሥልጣን ሳይኖራቸው ክፍያዎችን አጽድቀዋል በሚል መክሰሱ አመክንዮአዊ እንዳልሆነ አስረድተዋል።

በተጨማሪም የኦዲት ግኝቱን አስመልክቶ በተደረገው የመውጫ ስብሰባ (Exit Conference) ላይ እንዳይሳተፉ መደረጋቸውንና ትምህርት መማር እንደ ጥፋት ተቆጥሮ የቀረበው ውንጀላ በምን ዓይነት መመዘኛ እንደቀረበ ግልጽ እንዳልሆነ አመልክተዋል። የሦስተኛ ዲግሪ (PhD) ትምህርታቸውን በተመለከተ ቀደም ሲል ቅሬታቸውን ለዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት አቅርበው የነበረ ቢሆንም፣ ጉዳዩ በሥራ አመራር ቦርድ ፊት ቀርቦ ውሳኔ በሚጠበቅበት ሒደት ላይ እያለ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ይህንን ክስ ማንቀሳቀሳቸው በስተጀርባው ሌላ የተደበቀ ዓላማ እንዳለው ጠቁመዋል።

ዶ/ር አለሙ ጣሚሶ በስማቸው ላይ የተሰነዘሩት ከባድ የዲሲፕሊን ክሶች ዝርዝር ማብራሪያና ደጋፊ የጽሑፍ ማስረጃዎች በአስቸኳይ እንዲሰጣቸው በመጠየቅ ደብዳቤያቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ ለትምህርት ሚኒስቴር እና ለሀዋሳ ኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ በግልባጭ (CC) መላካቸውን ደብዳቤያቸው ያመለክታል።

በሌላ በኩል፣ አዲሱ አመራር ከተተካ ወዲህ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በአካባቢው ማኅበረሰብ ላይ ያነጣጠረ ጥቃትና መግፋት እየደረሰ እንደቆየና በርካታ የብሔሩ ተወላጅ አመራሮች ያለአግባብ ከሥልጣናቸው እየተነሱ እንደሆነ የሚገልጹ ቅሬታዎች በተደጋጋሚ እየተሰሙ ይገኛሉ።

Photos from Horn Insight's post 10/07/2026

በሲዳማ ክልል በተለያዩ ዞኖች ህገ-ወጥ የሠራተኛ ቅጥር እየተፈጸመ መሆኑ ተገለጸ

በሲዳማ ክልል በሰሜናዊ ሲዳማ ዞን ሀዌላ ወረዳ እንዲሁም በምስራቃዊ ሲዳማ ዞን ቦንሳ ወረዳ ውስጥ ተቋማዊ አሠራርን ያልተከተሉ ህገ-ወጥ የሠራተኛ ቅጥሮች እና የአሠራር ብልሽቶች እየተፈጸሙ መሆኑ ተገልጿል።

ከመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመርቀው የወጡ በርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል አጥተው ባለበት በአሁኑ ወቅት፣ በተለያዩ የወረዳ መዋቅሮች ውስጥ የሚገኙ አመራሮች ባለቤቶቻቸውን እና የቅርብ ዘመዶቻቸውን ያለአግባብ በሥራ መደቦች ላይ እየመደቡ መሆኑን የሚያሳዩ መረጃዎች በሰነድ ተደግፈው በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ይፋ ሆነዋል። ይህ ዓይነቱ አሠራር በብቃትና በግልጽ ውድድር ላይ መመስረት የነበረበትን የመንግሥት የሠራተኛ መዋቅር ያዛባ በመሆኑ በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታን ፈጥሯል።

ሆርን ኢንሳይት ጉዳዩን ይበልጥ ለማጣራት ወደ ሀዌላ ወረዳ ስልክ በመደወል ምላሽ የጠየቀ ሲሆን፣ ከሥራ ኃላፊዎች የተሰጠው ምላሽ በማህበራዊ ሚዲያ ከተሰራጨው መረጃ ጋር በከፊል የተለየ ሆኗል። የወረዳው አመራሮች በሰጡት ማብራሪያ፣ የሠራተኛ ቅጥሩ የተከናወነው እንደሚባለው በዝምድና እና ባልተገባ ትስስር ሳይሆን የወረዳው ሲቪል ሰርቪስ ጽሕፈት ቤት አስቀድሞ ተገቢውን ማጣራት አድርጎ የፈጸመው መሆኑን ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ቅጥሩ ከተፈጸመ በኋላ በነበረው ሂደት በአሁኑ ወቅት የታገደ መሆኑንና ለተቀጣሪዎቹም ምንም ዓይነት ደመወዝ እንዳልተከፈለ አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል በማህበራዊ ሚዲያ የተሰራጨው ሰነድ ግን ቅጥሩ የጥቅም ትስስር ያለበት መሆኑን በመጥቀስ፣ የሰሜናዊ ሲዳማ ዞን አስተዳደር እና የክልሉ መንግሥት የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስዱ የሚጠይቅ ነው።

በተመሳሳይ መልኩ በቦንሳ ወረዳ የውድድር መስፈርቶችን በጣሰ መልኩ 63 ሰዎች ያለምንም የቅጥር ማስታወቂያ በወረዳው አስተዳደር እና በፋይናንስ ኃላፊዎች ምስጢራዊ ስምምነት መመደባቸው እንዲሁም በአንድ የዞኑ ከፍተኛ አመራር የጥቅም ትስስር አማካኝነት የግለሰቡ ልጅ ሳይሠራ ደመወዝ ሲወስድ እንደነበር ተገልጿል።

ሆርን ኢንሳይት ወደ ምስራቃዊ ሲዳማ ዞን እና ቦንሳ ወረዳ የሥራ ኃላፊዎች ደውሎ ምላሻቸውን ለማካተት ያደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ በአሁኑ ወቅት ሳይሳካ ቀርቷል።
እነዚህ ተቋማዊ የአሠራር ግድፈቶች የክልሉን መልካም አስተዳደር አደጋ ላይ የጣሉ በመሆናቸው፣ የሚመለከታቸው አካላት የችግሩን ጥልቀት መርምረው ምላሽ መስጠት እንደሚገባቸው እየተገለጸ ይገኛል።

ሆርን ኢንሳይት የሁለቱንም ወረዳዎች ቀጣይ ተቋማዊ ምላሽ ተከታትሎ የሚያቀርብ ይሆናል።

09/07/2026

የክረምቱ ጎርፍ የፈጠረው የአዲስ አበባው አዲስ የስራ ዘርፍ

በኢትዮጵያ ወቅታዊው የክረምት ዝናብ መግባቱን ተከትሎ፣ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ የተለመዱት የጎርፍ ፈተናዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ የከተማዋን ወጣቶች ንቁ የፈጠራ አእምሮና ማኅበራዊ መስተጋብር የሚያሳዩ አስገራሚ ታሪኮችም እየተከሰቱ ነው። ሰሞኑን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በሰፊው መነጋገሪያ በሆነው ተንቀሳቃሽ ምስል (ቪዲዮ) ላይ በግልጽ እንደሚታየው፣ አንድ ቆራጥና ብልህ ወጣት በጎርፍ የተጥለቀለቁ የከተማዋን መንገዶች መሻገር የከበዳቸውን እግረኞች በጀርባው አዝሎ ሲያሻግር ይታያል።

ይህ ወጣት እግረኞች ውድ ጫማቸውና ልብሳቸው በጭቃና በቆሸሸ ውሃ ሳይበላሽ፣ ክብርና ውበታቸውን እንደጠበቁ ወደ ፈለጉበት ቦታ እንዲሻገሩ ያደርጋል። ለዚህ የጉልበትና የፈጠራ ስራው ደግሞ ተመጣጣኝ ክፍያ ይቀበላል። ይህ ለአንዳንዶች አስገራሚ፣ ለሌሎች ደግሞ አዝናኝ የሆነው የቢዝነስ አስተሳሰብ በከተማዋ ነዋሪዎች ዘንድ ትልቅ አድናቆትን አትርፏል። የክረምቱ ወቅት በመጣ ቁጥር የዋና ከተማዋ የመሠረተ-ልማት ክፍተቶች የራሳቸውን ፈተና ይዘው መምጣታቸው ባይቀርም፣ የከተማዋ ወጣቶች ግን ችግሩን ወደ መልካም የገቢ ምንጭነትና መፍትሔ አቅራቢነት የሚቀይሩባቸው እንዲህ ያሉ ጥንካሬዎች መደመጣቸውን ይቀጥላሉ።

Want your business to be the top-listed Media Company in Hawassa?
Click here to claim your Sponsored Listing.

Telephone

Website

Address


Hawassa