Fre Habeshawit

Fre Habeshawit

Share

Photos 29/05/2020

~~~~~~~~~~~~~~እጆቹ~~~~~~~~~~~~~~
ከስድስት ምዕተ አመታት በፊት ኑረምበርግ ከተማ አጠገብ ባለች አንድ ትንሽ መንደር ውስጥ አስራ ስምንት ልጆች ያሉበት አንድ ቤተሰብ ይኖር ነበር፡፡ ለዚህ ሁሉ ልጅ ምግብ ለማቅረብ አንጥረኛ የሆነው አባወራ በቀን አስራ ስምንት ሰአት በሙያው እና ከሙያው ውጪ መስራት ነበረበት፡፡
የቤተሰቡ የኑሮ ሁኔታ የከፋ ቢሆንም ከልጆቹ ውስጥ ሁለቱ ታላላቆች ልዩ ህልም ነበራቸው፡፡ ስነ-ጥበብ ማጥናትና ዝነኛ ሰዓሊ መሆን አባታቸው ኑረምበርግ ወደሚገኘው የስነ-ጥበብ አካዳሚ ልኮ ሊያስተምራቸው የሚያስችል የገንዘብ አቅም እንደሌለው ግን ሁለቱም ያውቁ ነበር ፡፡
አንድ ምሽት በተጨናነቀው አልጋቸው ላይ ሆነው በህልማቸው ዙሪያ ለረጅም ሰዐት ተወያዩና ወደ ስምምነት ደረሱ እጣ ሊጣጣሉም ወሰኑ በእጣው የተሸነፈው በአቅራቢያቸው ወደሚገኘው የማዕድን ማውጫ ሄዶ እንዲሰራ በሚያገኘውም ገቢ ወደ ከፍተኛ ትምህርት የሚሄደውን ወንድሙን እየረዳ እንዲያስተምር፡፡ እጣ የወጣለት ወንድም ደግሞ በኑረምበርግ ከተማ በሚገኘው ከተማ በሚገኘው የሥነ-ጥበብ አካዳሚ የአራት አመት ትምህርቱን እንዲማርና ትምህርቱንም ሲጨርስ በሚመረቅበት የሥነ-ጥበብ ሙያ ከሚሰራቸው ስዕሎች ሽያጭ በሚያገኘው ወይም አስፈላጊ ከሆነ እሱም በማዕድን ቁፋሮ ስራ ተቀጥሮ በተራው ያስተማረውን ወንድሙን ሊያስተምር ውሳኔ ላይ ደረሱ፡፡
አንድ እሁድ እጣው ተጣለ ታላቁ አልብሬሽት ዱረር የተባለው ወንድም እጣው ወጣለት ኑረምበርግ ከተማ ወደሚገኘው የስዕል አካዳሚ ገባ፡፡ እጣ ያልወጣለት ወንድም ወደ አደገኛው የማዕድን ቁፋሮ ስራ አመራ ለተከታዮቹ 4 አመታትም ወንድሙን በገንዘብ እየረዳ አስተማረ አልብሬሽት የአካዳሚው የስዕል ትምህርት ተዋጣለት፡፡ በልዩ ልዩ የስዕል ስራዎች የተካነ ሆነ የሚሰራቸው የቅብ ስዕሎች ከመምህራኑ ስዕሎች ይልቅ የላቁና እየተወደዱ መጡ፡፡ በኮሚሽን ለሚሰራቸው ስዕሎች ዳጎስ ያለ ገንዘብ ይከፈለው ጀመር፡፡ ወጣቱ ሰዐሊ ትምህርቱን አጠናቆ ወደ መንደሩ ሲመለስ ቤተሰቡ በድል መመለሱን ምክንያት በማድረግ ድግስ ደግሶ ጠበቀው፡፡ በሙዚቃና በሳቅ በደመቀው ግብዣ መጨረሻ ላይ ሰአሊው አልብሬሽት ከክብር ወንበሩ ተነሳና ለተወዳጅ ወንድሙ ለአመታት ስለከፈለው መሰዋእትነት ህልሙንም እንዲያሳካ ስለረዳው ጽዋ አነሳ፡፡ በመዝጊያ ንግግሩም "የተባረክህ ወንድሜ አልበርት ሆይ አሁን እንግዲህ ተራው ያንተ ነው ወደ ኑረምበርግ ትሄዳለህ አንተም ህልምህን ታሳካለህ እኔም በተራዬ እንከባከብሀለው"አለ፡፡ በገበታው የታደሙት ሁሉ አንገታቸውን ከገበታው አንድ ጥግ ላይ ወደ ተቀመጠው የማዕድን ሰራተኛ አዞሩ ፡፡ በገረጣው ፊቱ ላይ እንባው እየተንከባለለ በጉንጮቹ ላይ እየፈሰሰ ነው ራሱንም ከግራ ወደ ቀኝ እየወዘወዘ ሳግም እየተናነቀው ደጋግሞ "አይሆንም አይሆንም ወንድሜ ሆይ.....አይሆንም" አለ፡፡ በመጨረሻ ብድግ ብሎ እንባውን ከጉንጮቹ ላይ በማበስ አሻግሮም በገበታው ላይ የታደሙትን የሚወዳቸውን ፊቶች በፍቅር እየተመለከተ ሁለት እጆቹን አጣምሮ ወደ ቀኝ አገጩ በማስጠጋት ለስለስ ባለ ድምፅ "የለም ወንድሜ ሆይ ኑረምበርግ ልሄድ አልችልም ለእኔ ዘግይቷል የአራት አመት የማዕድን ቁፋሮ ስራ እጆቼን ምን እንዳደረጋቸው ተመልከትማ! በጣቶቼ ላይ ያሉ አጥንቶች ሁሉ ቢያንስ በቀን አንድ ጊዜ ይጎዱ ነበር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በከባድ የቁርጥማት በሽታ እየተሰቃየሁ ነው በእርሳስ እና በብሩሽ ሸራ ላይ ስዕሎችን መቀባት ይቅርና አላስተዋልከኝም እንጂ ፅዋችንን እናንሳ ስትል ፅዋውን ለመያዝ እንኳ የቀኝ እጄ አልቻለም፡፡ ለእኔ ዘግይቷል" አለ፡፡
ይህ ታሪክ ከተፈፀመ 450 ዓመታት በላይ አልፎታል፡፡ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ የአልብሬሽት ዱረር እፁብ ድንቅ ሰራዎች የራስ ምስሎች የእርሳስና የውሀ ቀለም ቅቦች የቻርኮል ስራዎች የእንጨት ቅርፃ ቅርፆች የመዳብ ወቅሮች በመላው አለም ባሉ ሙዚየሞች ተሰቅለው ይገኛሉ፡፡ ይሁን እንጂ ብዙ ሰዎች ከሌሎች ስራዎች ይልቅ እጆቹ የሚለውን ስራውን ቅጂ በየቤቶቻቸውና ቢሮዎቻቸው ግድግዳዎች ላይ አንጠልጥለውታል፡፡
አንድ ቀን ወንድሙ ለከፈለለት መሰዋእትነት አክብሮት ለመስጠት አልብሬሽት ዱረር በከፍተኛ ጥንቃቄ የወንድሙን የተጎዱ እጆች መዳፎቹ ተገጣጥመው ቀጫጭን ጣቶቹ ወደ ሰማይ ተዘርግተው የሚታዪበትን ስዕል ሳለ፡፡ ይህንን ድንቅና ሀያል ስራውንም እጆቹ የሚል ስያሜ ሰጠው ፡፡ ብዙም ሳይቆይ በአለም ዙሪያ ስዕሉን የተመለከቱ ሁሉ ለዚህ ታላቅ ስራ ልባቸውን ከፈቱለት፡፡
ይህን በፍቅር የተነሳ የተሳለ ስዕልም "የሚፀልዩ እጆች" ብለው
ሰየሙት፡፡

21/04/2020

ኢትዮጲያ እጆቿን ወደ እግዚያብሔር ትዘረጋለች!!!

Want your establishment to be the top-listed Arts & Entertainment in Addis Ababa?
Click here to claim your Sponsored Listing.

Website

Address


Addis Ababa