MY PATH

MY  PATH

Share

08/12/2025

“የአባቴ ትዝታዎች“
ሰሞኑን የአባቴ የቅርብ ጓደኛ የነበረው ፣ ቆፍጣናውና በወታደራዊ ድስፕሊኑ የምኮራበት፣ ሻለቃ ኪዳኔ ፋሪስ ከዚህ ዓለም ድካም አረፈ። ያባቴን ጓደኞች ባሉበት እያነፈነፍኩ ጥቂቶቹን አገኝቻቸው አቃለሁ። ጋሸ ኪዳኔን ካንድም ሁለት ጊዜ ቤቱ ሄጀ ጠይቄዋለሁ። በአንድ ወቅት ጉርስም የሚባል፣ ሀረርጌ ጠ/ግዛት ውስጥ የሚገኝ የአንድ አውራጃ ከተማውስጥ፣ ሻለቃ አሰፋ ቴሊላ የተባለ መኮንን ቤትን ተከራይተን በግቢው ውስጥ ባሉት ቤቶች አብረን እንኖር ነበር። ጋሸ ኪዳኔን በጣም እወደው ነበር። ወደ ቀብሪደሃር ከተዛወርን በኋላም ቤቱ እየሄድኩ እጠይቀው ነበር። ሌላው የአባቴ ጓደኛ የነበረውን ሻምበል ተዘራን ደሴ ከተማ አገኝቸው ብዙ ጊዜ እንጠያየቅ ነበር። አሁን መልሸ ካገኘሁት ሦስት ዓመታት አልፏል። ጋሸ ተዘራ ከአባቴ ጋር ከሶማሊያ ጋር
ሲዋጉ፣ አባቴ በጦር ሜዳ ቢወድቅም፣ እሱና የቀረው 70 የማይሞላ አንድ ሻምበል ጦር፣ የገጠማቸውን 11,000 የሶማሌ ሰርጎ ገብ ጦር እስከ ባሌ/ ኤርከሬ የምትባል ሥፍራ ድረስ አሳደው እንደ ደመሠሡት ፣ከብዙ ዓመት በኋላ ስንገናኝ በዝርዝር አጫውቶኝ ነበር። የጋሸ ሻለቃ ኪዳኔ የሂወት ታሪክ ሲነበብ ዕድሜው 85 ዓመት እንደሆነ ሰምቻለሁ። ጋሸ ኪዳኔ ከአብዘሃኛዎቹ ወታደሮች በወቅቱ በጣም ወጣት ነበር። በዚህ ስሌት አብዘሃኛዎቹ የአባቴ ጓደኛቹ ቢያንስ በተፈጥሮ ሞት አልፈዋል ብየ አስባሁ። ያን ጊዜ ኢትዮጵያ ጦር በአሜሪካና እስራኤል በሚገባ የሰለጠነ 45,00 ወታደር እንደነበር እሰማ ነበር። ይህ ጀግና ሠራዊት በኮሪያና በኮንጎ ባደረገው ዘመቻ በዓለም አገራችንን ያኮራ ነበር።

እንግዲህ በመቀጠል አባቴን ደግሞ በጨረፍታ ልዘክረው።

አባቴ መፃፍና ማንበብ አይችልም፡፡1ኛ ደረጃ ተማሪ ሳለሁ ከትምህርት ቤት ስመለስ ደብተሬን እየተቀበለኝ ራይትና ኤክስ ያገነኋቸውን ይቆጥራል፡፡ ዛሬ ቀኑ ስንት ነው ይለኛል፡፡ ካርታ ሲጫዎት ቁጥሮችን ያውቃል፡፡ኮነጎ የሰማቸውን የስዋህሊ ቃላት፣"መታታ ማዙሪ" ሲል እሰማዋለሁ፡፡ ጂግጂጋ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ስማር ቆይቸ፣ ለዕረፍት ቀብሪደሀር ስመለስ ፣ ሶማሊያ ድንበር ጥሳለች ተብሎ ፣ ገላዲን ግዳጂ ሄዶ ጠበቀኝ፡፡ አለቆቹ ፣ ገላዲን ሮጆርስ ምሽግ ድረስ ወሰዱኝ፡፡ 15 ቀናት ምሽግ ውስጥ ቢራ ሲያጠጡኝ ከርሜ ካባቴ ጋር ቀብዲሃር አብረን ተመለሰን፡፡ 11ኛ ክፍል አልፌ ስመለስ ደግሞ ሽላቦ(ካሉብ) ለግዳጅ ሄዶ ጠበቀኝ፡፡ አባቴን እንዳየው ኮረኔሉ ካሉብ ወሰዱኝ፡፡ ሶማሊዎች የነዳጅ መመርመሪያ የሽቦ መስመሮችን ሌሊት ሌሊት እየበጣጠሱ አስቸግረው ስለ ነበር ኮረኔል የሚሄዱት የሶማሊ ሽማግሌዎች ጋር በዚህ ጉዳይ ላይ ለመወያየት ነበር፡፡ በርካታ ሽማግሌዎች ጫካ ውስጥ ተሰብስበው ጠበቋቸው፡፡ ሶማሌዎች አሳባቸውን ለመናገር ግልፅና ደፋሮች ናቸው፡፡ የመመርመሪያ ሽቦዎቹን የሚቆራርጧቸው የነዳጅ መርማሪ ድርጂቱ /ቴኒኮ እነሱን ሳይቀጥር ከአዲስ አበባ ሰው እያመጣ በመቅጠሩ ተናደው እንደሆነ ሽቦዎቹን የሚቆራርጡት በግልፅና በድፍረት ተናገሩ። ኮረኔሉም፣ ነዳጁ ሲገኝና ሲወጣ፣ ሙያቸው በሚፈቅድላቸው የሥራ መስክ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እንደሚቀጠሩ አስረዷቸውና ስምምነት ላይ ተደረሰ።
ካሉብ እንደደረስኩ ከአባቴ ጋር ምሽግ ውስጥ እናድር ነበር። ጥበቃ ላይ ሲሆንም እረዥም ግራር ላይ የተሰራ ማማ ላይ ተቀምጠን አባቴ ዘብ ይጠብቅ ነበር፡፡ አንድ ቀን አንድ ሶማሌ እጮኸ በጫካ ውስጥ ግመል እንደሚፈልግ ሰው ሲቅበዘበዝ አየነው፡፡ ወደ ድንኳኖቹ ሲያመራ አባቴ ተመለስ አላለውም፡፡ ድንኳኖቹ ውስጥ ሰተት ብሎ ሲገባ ከማማው ላይ ወርዶ በቁጥጥር ሥር አዋለው፡፡ ከሶማሊያ መንግሥት የተላከ ሰላይ ነበር፡፡
ከ15 ቀናት በኋላ አባቴ እንዲሸኜኝ ተፈቅዶለት ቀብሪደሃር ተመለስን፡፡ አንድ ቀን ሊጋብዘኝ ወደ ከተማ ሄደን ቡና ቤት ግቢ ዳስ ውስጥ ብቻችንን ተቀመጥን፡፡ አነድ ካሴት ቢራ አስመጥቶ አሸዋ ውስጥ አስቀብሮ በላዩ ላይ፣እንዳይሞቅ ውሃ አሰደፋበት፡፡ ቢራው ቢከፈትልንም የምጠጣው እኔ ብቻ ነበርኩ፡፡ ከቡና ቤቱ ጀርባ ጠጅ ቤት ስለ ነበር የሰዎች ሁካታ ይሰማል፡፡ አባቴ አስርየ ወደ ጠጅ ቤቱ እየሄደ ይመለሳል፡፡ ግራ ገባኝና ፣ ምን ሆነህ ነው የምትመላለሰው አልኩት፡፡ ጓደኞቼ ጋር ጠጅ አስቀድቼ ተጎንጭቼ እየመጣሁ ነው አለኝ፡፡ ምን ችግር ገጥሞህ ነው ላንድ ነፍስህ ጠጅ የምትጠጣው አልኩት፡፡ አይ ልጄ ቢራ ብጠጣ ጓደኛ አገኝ መሰለህ አለኝ፡፡ ጓደኞቹን በጣም ይወዳቸዋል፡፡ ሲቸግራቸው ቢያጣ እንኳን ተበድሮ ገንዘብ ይደርስላቸዋል፡፡ ሲበደሉ ግንባር ቀደም ጠበቃቸው ነው፡፡ ወታደሮች ሲደባደቡ ከደረሰ፣ መጀመሪ በዳዩን ከዛፍ ላይ ቅርንጫፍ ገንጥሎ ይመታውና፣ ተመችውንም፣ ምን ሆነህ ነው አንተስ የምትመክተው ብሎ ሳይዠልጠው አይተወውም፡፡ እኔም ከልጆች ጋር ስጣላ ታናናሾቸን እንድመታ አይፈቅድልኝም እንጂ፣ ታላላቆቸን ግን ቢመቱኝም ብመታቸውም አይቶ እንዳላየ ዝም ይለኛል፡፡ ሁለት ጊዜ ታላላቆቼን ፈንክቼ ካሳ ከፍሏል፡፡ ለምን መታህ ብሎኝ አያቅም፡፡ እሱም መቶኝ አያቅም፡፡አለቆቹ ይህን ባህሪውን ተው ብለው ይመክሩታራል፡፡ ጓደኞቹ ሻምበልና ሻለቃ ማእረግ ሲደርሱ እሱ በአሥ/ አ/ ማዕረግ ነው ጦር ሜዳ የተሰዋው፡፡ ማእረጉ የተሰጠውም እኔን አስተምሮ ለመምህርነት ስለ አበቃኝ እንደሆነ ጓደኞቹ ነግረውኛል፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ደርሸ ሥራ እስከምይዝ ድረስ ወንደላጤ ሆኖ ነው ያስተማረኝ።
ከአስመራ ቀብሪደሃር ስመለስ፣ ከስር ቤት ተፈታ፡፡ ለግዳጅ ደገሀቡር ሄዶ ሳለ አንድ ወታደር ሰክሮ ሚሊታሬ ፖሊሶች ወደ ካምፕ እየመለሱት ሳለ፤መንገድ ላይ አልሄድም ብሎ ያስቸግራቸዋል፡፡ ደብድበውት ሲጮህባቸው በአፉ አሸዋ ሲጨምሩ ይደረሳል፡፡ የመንግሥት ወታድር እንዴት እደዚህ ታደርጋለችሁ ብሎ ካባረራቸው በኋላ ወታደሩን አዝሎ ወደ ካምፑ እየወሰደው ሳለ፣ፖሊሶቹ ሃይል ጨምረው ተመልሰው ከበው በቁጥጥር ስራ አዋሉት፡፡ በአድራጎቱ ተከሶ 42 ቀን እስራት ተፈርዶበት ወደ ክፍሉ ላኩት፡፡ መምጣቴ ሲሰማ ነበር የተፈታው፡፡ ሰውነቱ ግዙፍና ጠናካራ ነበር፡፡ መቶ ሜትር እሩጭ ስንወዳደር ፈፅሞ አልቀድመውም፡፡ ምኞቱ ጀነራል እንድሆንለት መሆኑን ያወቅሁት ዘግይቸ በመምህርነት ከተመረቅሁ በኋላ ነበር። ያሳደገኝ እንደ ወታደር አድርጎ ነበር። ለአባቴ ክብርና ደግነቱን እንድናገር ፍቅዱልኝ። ይህ አባቴ የምላችሁ የ7ዓመት ህፃን ሳለሁ ሚስቱ ከእናቴ ጉያ የሰረቀችኝና አንቀባሮ ያሳደገኝ ደጉ ወታደር ነው እኮ። እኔም የሡ ህያው የደግ ሠው ሃውልት ሆኜ በሥሙ ኃይሉ ገብረፃድቅ እየተባልኩ አጠራለሁ። ልጆቸም እስከ አያታቸው ሲጠሩ የእሡ ሥም ይጠራል። አባቴ ከዘመዶቸ ጋር ካገናቸኝ በኋላ በጦር ሜዳ ተሠዋ። ለዚህ ነው የጓደኞቹን ህልፈት ስሠማ የማለቅሠው።

08/11/2025

(ይህን ከለጠፍኩት ቆይቻለሁ፣ ካገኘሁት አይቀር ብየ ፣ አርታኢ አድርጌ መልሸ ለጥፌዋለሁ )

"የአዲስ መንግሥት ፈተና "

ኪንጊስለይ ዴቪድ የተባለ ምሁር በማህበራዊ ጉዳይ ጥናቱ ላይ፣ በሦስተኛው ዓለም አገሮች አምገነን መንግሥታት በአመክኝ በየ 15 ዓመቱ ከነሱ በፊት ያነበረውን መንግሥት በኃይል እያሶገዱ የመንግሥት ሥልጣን ይቆጣጠራሉ ይላል። ለምሣሌ፣ ከደርግ ብንጀምር፣ የንጉሡን መንግሥት አሶግዶ 17 ዓመት ገዛ፣ ኢህአዴግ ደግሞ ደርግን አሶግዶ 27 ዓመት ገዛ። ከአቶ ኃይለማሪም መንግሥት አስከ አለንበት መንግሥት ጊዚ 11 ዓመት ገደማ መሆኑ ነው። (የመጨረሻዎቹ ሁለትቱ መንግሥታት መሃል የሃይል የመንግሥት ሽግግር ባለመኖሩ እንደ አንድ መንግሥት ስለ ወሰድኳቸው ነው።) የሦስቱን መንግሥታት የመንግሥትነት ቆይታ ዕድሜ ስንደምር 55 ዓመት ይሆናል። የሦስቱን መንግሥታት የቆይታ ዕድሜ ለ 3 ስናካፍል፣ የኪንግሥሌይን አማካይን አማካይ የዓመታት አማካይ የዕድሜ ቁጥርን ( 15 ዓመትን ) እናገኛለን።
ኪግስሌይ የመንግሥታቱን የቆይታ ዕድሜ አዙሪት ባህሪ ሲተነትን፣ አዲስ የፖለቲካ ሃይል ስልጣን ኮርቻ ላይ ሲቆናጠጥ ከሚያጋጣሙት ችግሮች መሃል አንዱ ፣ የአዲሱን መንግሥት የቢሮክራሲ ማሺነሪ የሚሞላበት ታማኝና ብቃት ያለው የሰው ሃይል የማግኘት ችግር ነው፣ ይላል፡፡
ለምሳሌ የኢህአዴግን መንግሥት እንይ። አቶ መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት፣ “አንዳንድ ምኒሰትሮችዎ ብቃት የላቸውም፣” ተብለው ሲጠየቁ፣ ለድርጂታችን ታማኝ ይሁኑ እንጂ ለእኛ ዘበኛም ቢሆን ሃላፊነት ላይ ሊቀመጥ ይችላል ፣ እንዳሉት ማለት ነው ፡፡ ታዲያ ኪግስሌይ ዴቪድ እንደጻፈው ፣ አዲሱ መንግሥት ስልጣን ላይ እንደወጣ የቢሮክራሲውን “ማሽነሪ” ለውጡን በሚደግፍ የሰለጠነ የሰው ሃይል ለመሙላት ቢፈልግም ፣ ብቃት ያላቸው ምሁራን፣ የአዲሱን መንግሥት ማንነት ጊዜ በመውሰድ ፈትሸው እስከሚያውቁ ድረስ በጥርጣሬ ውስጥ ሆነው ከዳር ቆመው ለተወሰነ ጊዜ ይባክናለሰ ፡፡ አዲሱ መንግሥት ደግሞ አገር የመምራት ሥራው ጊዜ ስለ ማይሰጠው ብቃት ያላቸውን ምሁራን በቢሮክራሲው ገብተው እስከሚያግዙት አይጠብቅም ፡፡ ይልቁንም የቀረቡለትን አነስተኛ ብቃት ያላቸውን (mediocre ) ሁሉ እያግበሰበሰ በቢሮክራሲው “ማሺኔሪ” ውስጥ ይሰገስጋቸዋል ፡፡
እነዚህ ብዙም ብቃት የሌላቸው ሰዎችም ቢሆኑ፣ አጋጣሚውን በመጠቀም ፣ በአዲሱ መንግስት መዋቅር ውስጥ በመግባት ተጠቃሚ ለመሆን ይጣደፋሉ፡፡
አዲሱ መንግስት ብቃት ላላቸውን ምሁራን፣ ህዝባዊ መንግሥት መሆኑን በተግባር እያሳየ ካልመጣና ቀስ በቀስ የሰገሰጋቸውን ብቃት የሌላቸውን ሰዎች ብቃት ባላቸው ካልተካ ከባድ አደገ ያጋጥመዋል። ብቃት የሌላችው ቢሮክራቶች በህዝብ ላይ በርካታ የአስተዳደር በደሎች ከማድረሳቸውም በላይ ቀድሞውንም ለጥቅም ሲሉ ወደ መንግሥት ማሽነሪው የተሰገሰጉ በመሆናቸው በሙስና ተግባር ላይ ተዘፍቀው በሀገርና ህዝብ ላይ በደሎችን እየፈጸሙ በሄዱ ቁጥር፣ አዲሱን መንግስት በጥርጣሬ ሲያጠኑት የነበሩት ምሁራን እራሳቸውን ከመንግሥት ከማራቅ አልፈው መንግስትን ከሚቃወሙ የተደራጁ ሃይላት ጋር እየወገኑ ይመጣሉ፡፡ ህዝብም በዘቀጠው የቢሮክራሲ ተግባር እያደር መንግሥትን እያማረረ እና እየጠላ፣ ብሎም እየተቃወመ፣ ይመጣል። የተቃዋሚ ሃይላትም በዚህ አመቺ ነባራዊ ሁኔታ እየተደገፉ የትግል ጡንቻቸው እየፈረጠመ ይሄዳል ፡፡ አዲሱ መንግሥትም አዲስ መሆኑ ቀርቶ እያረጃ ይመጣል፡፡
በዚህ ደረጃ ላይ እነዚያ አስቀድመው በመንግድስት መዋቅር ውስጥ ተሰግስገው ህዝብን ሲያስመርሩ የነበሩት እበላ ባዮችና አደር ባዮች፣ “ ወንድምዬ ምንድን መላው ፣አይተን ጊዜውን ወደ ሚያደላው ፤” እንደተባለው የገበሬዎች የዘፈን ብሂል፣ አሰላለፋቸውን ከአዲሱ ሃይል ጋር ማስተካከል ይጀምራሉ፡፡ የነበሩበትን መንግሥትንም ከሳሽ ከመሆናቸውም በላይ በሥራ አጋጣሚ እጃቸው የገባውን የመንግሥትን የሰነድ ሚስጢር እያሾለኩ የአዲሱ የመንግሥት ተቃዋሚ ሃይል አሳልፈው በመስጠት ፣በድል አርበኝነት፣ ከአዲሱ መንግሥት ጋር ለመቀላቀል ይሞዳሞዳሉ፡፡
የ “ኢህአዴግ ስልጣን የዛፍ ላይ እንቅልፍ ነው፣ “ ሲባል የነበረውን አባባል፣ ቀደም ባሉት ዓመታት ኢህአዴግ ስልጣን እንደጨበጠ፣ በመዋቅሩ የተሰገሰጉትን ብቃት የሌላቸውን የቢሮክረሲ ሰዎች ለማጥራት የሚሰራ ይመስለኝ ነበር። እያደር ስመለከት ግን ከአንዱ መስሪያ ቤት አንስቶ እሌላ መስሪ ቤት ፣ ከአንዱ አካባቢ አንስቶ እሌላ አካባቢ የማዟዟር አሰራር በመከተል ሙሰኞችን እና ዋልጌዎችን ማሽሞን ያዘ። በመጨራሻም እራሱን "በስብሻለሁ " የሚልበት ደረጃ ላይ አደረሰ። “በአብዮታዊ ዲሞክራሲ” የፖለቲካ ፈሊጥ፣ “ከእኛ ጋር ካልሆኑ ጠላቶቻችን ናቸው፣” በሚለው አሰራር አገሪቱን ጠላትና ወዳጅ በሚል ጎራ ከፋፈለ። የኢህዴግ አባል የሆነ ሁሉ ችሎታ ባይኖረውም በየመንግሥት መስሪያ ቤት አለቃ እየሆነ ተሠገሠጉ። ኢህአዴግ በውስጡ በተሰገሠጉ ሙሰኞች ተቦርቡሮ ሲዳከም ፣"በስብሻለሁ፣" እስከማለት ቢደርስም ፣ የዕርምት እርምጃ ግን ለመውሰድ ተሳነው። በመጨረሻም ኪንግስሌ እንዳለው፣ አራቱ የኢሃዴግ አውራ ድርጂቶች የቀደመ አደረጃጀታቸውን አፍረሰውና ቀንደኛውን ህወሃት ከመሃላቸው ወጥተውና የዳር ተመልካች የነበሩት አጋር ድርጂቶች በአባልነት ተቀብለው፣ አዲስ፣ ግን ኢህአዴግን የመሠለ፣ ሥርዓተ መንግሥት ተተካ። የተተካውም መንግሥት ከቀደመው መንግሥት የተለየ አይመስለኝም፣ በእኔ አመለካከት። ምክንያቱም፣ እንደ ቀደመው ኢህአዴግ የየክልሉ ፓርቲዎች በአዲሱ ፓርቲ ውስጥም ፍፁም የተዋሃዱ ፓርቲዎች ሳይሆኑ፣ ስብስቦች ( aggrommerated Parties) ስለ ሚመስሉኝ ነው። ይህ ያልተዋሃደ ፓርቲ፣ በብሔር/ ብሄረሰቦች ክልል በተከፋፈለች ሀገር ውስጥ ሠላምን አስፍኖ ሀገሪቱን በልማት ወደ ፊት ለማራመድ ያመቸዋል ብሎ ተስፋ ለማድረግ ያዳግታል፣ ሁሉም ኢትዮጵያን ከራሱ ክልል እኩል ስለማያይ።
ኪንግስሌ የሚለው አዙሪት ቢከሰትስ ሀገራችን ምን ታተርፋለች።
ደግሞ ሌላ አዙሪውሰት ውስጥ ላለመውደቅ ምን ዋስትና አለን?

በመጨረሻ፣ " ሀገሬ ሠው አጣሽ ወይ ?" በሚለው የነዋይ ደበበ ጥሪ እደመድማለሁ።

Want your public figure to be the top-listed Public Figure in Dessie?
Click here to claim your Sponsored Listing.

Telephone

Website

Address

Dessie