Amba 27
በሁለት ጆሮዋ የምትሰማ ብቸኛ ፍጥረት ማን ናት?
ላለመሳቅ ይሞክሩ
22/06/2024
† ግልጽ ደብዳቤ ለቅዱስ ሲኖዶስ †
† ታላላቅ በዓላትን አናደብዝዛቸው።†
★ በዓለ ጰራቅሊጦስ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ቀን ተብሎ መሰየሙ ትክክል አይደለም። ፕሮቴስታንቱ በፓርላማ በዓለ ሃምሳ ብለን እንድናከብር ካላንደር ይዘጋጅልን የሚሉት ይህንን ታላቅ ቀን በገዛ እጃችን እያደበዘዝን ነው።★
† በዓለ ሃምሳ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከትንሣኤ በኋላ በሃምሳኛው ቀን የሚከበር ብሔራዊና ሃይማኖታዊ በዓላችን ነው።†
መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉ በአግባብና በሥርዓት ይሁን ይላል።1ቆሮ 14፥40 ቀደምት ኦርቶዶክሳውያን አባቶች እያንዳንዷን ዕለት ሲሰይሙና ሥርዐት ሲደነግጉ በብዙ ጥንቃቄና ማስተዋል ተመልተው ነው። በዓላትን ሲሰይሙ በዕለቱ ሊታሰብ ስለሚገባው የቀኑ ባለቤት ሰፊና ጥልቅ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያለው ይትባሃል ደንግገው ነው።በእያንዳንዷ ዕለት በቤተክርስቲያን ውስጥ የሚሰጡ አገልግሎቶች በሙሉ የቀኑን ባለቤት የሚያዘክሩ ናቸው።በማኅሌት፣በሰዓታትና በቅዳሴ፣በስብከተ ወንጌልና በዝማሬ የሚተላለፈው መንፈሳዊ መልዕክት ሁሉ ዕለቱን መሠረት ያደረገ ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በጠቅላይ ቤተክህነት በኩል ያለው ግዴለሽነትና በቀደሙ አባቶች መንገድ አለመሄድ የቤተክርስቲያኒቱን ክብር በማይመጥን መንግድ ከሥርዓት የወጡ እንግዳ ድርጊቶች ሲፈጸሙ እየተመለከትን ነው።
ሁላችን እንደምናውቀው ጰራቅሊጦስ ከቅድስት ሥላሴ አንዱ አካል የሆነው መንፈስ ቅዱስ ነው።መንፈስ ቅዱስ ደግሞ የቤተክርስቲያን ሕይወት ነው።እያንዳንዱ ምሥጢራተ ቤተክርስቲያንና ልዩ ልዩ አገልግሎቶች ሁሉ የሚከናወኑት በመንፈስ ቅዱስ ጸጋና ኃይል ነው።ያለ መንፈስቅዱስ እገዛ ቤተክርስቲያን የምታከናውነው አንዳችም ዓይነት አገልግሎት የለም።ይሁን እንጂ ለመንፈስ ቅዱስ የሰጠነው ቦታና ክብር ልንሰጠው የሚገባውን ያህል መንፈሳዊ ደረጃውን የጠበቀ አይደለም።
ለምሳሌ ያህል እግዚአብሔር አብ ብለን የሰየምናቸው በርካታ አብያተ ክርስቲያናት በመላ ሀገሪቱ ሞልተዋል፣በእግዚአብሔር ወልድ ስም የተሰየሙ አብያተ ክርስቲያናትም እጅግ በርካቶች ናቸው፤ በመንፈስ ቅዱስ ስም የተሰየመ የጰራቅሊጦስ ቤተክርስቲያን ግን ፈልጎ ማግኘት እጅግ ከባድ ነው።መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ ጋር በሥልጣን በአገዛዝና በመለኮት አንድ የሆነ የራሱ የሆነ ፍጹም መልክ፣ፍጹም ገጽ ፣ፍጹም አካል ያለው እግዚአብሔር ነው ብለን በምሥጢረ ሥላሴ አስተምህሯችን እስካስተማርን ድረስ ለመንፈስ ቅዱስ ልንሰጠው የሚገባው ክብርና ቦታ ከአብና ከወልድ ያልተናነሰ እኩል የሆነ አገልግሎት ሊሆን ይገባል።አሊያ መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ ያንሳል የሚለውን የመቅዶኒዮስን ስሑት ሐሳብ በቃል እየተቃወምን በተግባር ግን እየተከተልን ነው።
እንዲህ ለማለት የተነሳሁበት ምክንያት በአዲስ አበባ ጎላ ሚካኤል ተብሎ የሚጠራው ቤተክርስቲያን ሲመሠረት የጰራቅሊጦስ ቤተክርስቲያን ነበር፤ ነገር ግን ስለመንፈስ ቅዱስ ክብር፣በመንፈስ ቅዱስ ስለሚገኘው ኃይልና ጸጋ ፣ስለ መንፈስ ቅዱስ ልዩ መለኮታዊ አሰራር በሚገባ ሕዝቡን ስላላስተማርን ወደዛ ቤተክርስቲያን የሚሄደው ሕዝብ ጥቂት ስለሆነባቸው ካህናቱ የሚካኤልን ታቦት አስገብተው ሕዝቡን ሚካኤል መጥቶላችኋል እያሉ ስለሰበኩት እጅግ በርካታ ሕዝብ መሄድ ጀመረ በዚህም የተነሳ ጎላ ሚካኤል ተባለ።ከመንፈስ ቅዱስ ይልቅ ሚካኤል ጎልቶ እንዲታይ ያደረገ ትምህርትና ሥርዓት ሕዝቡን በማስለመዳችን እስከዛሬ ድረስ ጎላ ሚካኤል ሲባል ይጠራል።ደብሩ ተሰይሞበት የነበረው ጰራቅሊጦስ ግን በዓመት አንዴ እንዲታሰብ ቢደረግም እስከዛሬ የሚካኤልን ያህል ክብርና ቦታ አላገኘም።
ወገኖቼ በጣም እናስተውል ቅዱሳን መላዕክትን ማክበር በጣም ተገቢ ነው።ምልጃና ጸሎታቸው እንዲያግዘን መማጸንና ጥበቃቸው እንዳይለየን መትጋት ሁላችን ልንጠብቀው የሚገባ ኦርቶዶክሳዊ ሥርዓታችን ነው፤ ነገር ግን አምላክ የሆነውን መንፈስ ቅዱስን ከመልአክ በታች አሳንሰን ተገቢውን ሥፍራ አለመስጠት ፍጹም ስህተት ነው። ይህ ሁሉ የትምህርት እጥረትና ከእግዚአብሔር ክብር ይልቅ ገንዘብ የሚያስገኝልን የትኛው ነው በሚል ሥጋዊ አስተሳሰብ የሚመጣ ኢኦርቶዶክሳዊ አካሄድ ስለሆነ የቤተክርስቲያኒቱ የበላይ አካል የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስና ጠቅላይ ቤተክህነት እንዲህ ዓይነት ነገሮችን አጥብቆ ሊያስተካክል ይገባል።
እጅግ የሚያሳዝነው የቤተክህነቱ ቸልተኝነትና ግዴለሽነት በዚህ ሳያበቃ በዓመት አንዴ የሚታሰበውን በዓለ ጰራቅሊጦስ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ቀን በሚል ሌላ ግርዶሽ መከለሉ እጅግ ያሳፍራል።ቀደምት አባቶች በዓለ ጰራቅሊጦስን እንድናስብ ሥርዓት ሲሰሩልን በዕለቱ ስለመንፈስ ቅዱስ አሰራር፣ስለ መንፈስ ቅዱስ ኃይልና ሥልጣን ፣ስለመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በሰፊው ትምህርቶች እንዲሰጡ፣ለመንፈስ ቅዱስ ዝማሬና ቅኔ ከወትሮ በተለየ እየቀረበ ዕለቱን እንድናስብ ነበር።አሁን ግን ይህ ሁሉ እንዲድበሰበስና እንዲኮስስ የሚያደርግ ሥርዐት እየተሰራ መሆኑን እያየን በመሆኑ በፍጥነት ሊስተካከል ይገባል።ምክንያቱም በጊዜ ሂደት ልክ እንደ ጎላ ሚካኤል መንፈስ ቅዱስ እየተረሳ ይሄድና የሰንበት ትምህርትቤቶች ሪፓርትና የሥራ ዕቅድ የሚቀርብበት የስብሰባ ቀን ሆኖ ይቀራል።
አንባብያን እዚህ ላይ በጣም አስተውሉ የሰንበት ትምህርትቤቶች ቀን ማሰብ ተገቢነው።ነገር ግን ቀኑ በመንፈስ ቅዱስ በዓል ላይ መደረብ የለበትም።የሰንበት ትምህርትቤቶች ቀን እኮ ትልቅ ቀን ነው።በዕለቱ ስለ ሰንበት ትምህርት ቤት ጥቅም፣በሰንበት ትምህርት ቤት ስላለፋ አባቶችና መምህራን የሥራ ፍሬ በስፋት የሚዘከርበት እንዲሁም ወጣቶች ወደ ሰንበት ትምህርት ቤት እንዲመጡ ሰፊ ቅስቀሳና የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት የሚተላለፍበት ቀን ነው።ታዲያ ሁለት ታላላቅ በዓላትን አንድላይ ማደራረብ ፍጹም ስህተት ነው።
ፕሮቴስታንቱ ፓርላማ ውስጥ ለመንግሥት እያቀረቡ ያለውን ጥያቄ ሁላችን ተከታትለናል።በዓለ ሃምሳ የሚባል ቀን በካላንደር የሚዘጋ ዕለት ያስፈልገናል ብለው እየተሟገቱ ነው።ይህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ክብርና ሉዓላዊነት የሚገፋ ጥያቄ ነው።ምክንያቱም በዓለ ሃምሳ ከትንሣኤ በኋላ በሃምሳኛው ቀን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዐት የሚከበር ብሔራዊ ሃይማኖታዊ በዓላችን ነው።ስለዚህ ሉዓላዊ ክብራችንን ማስደፈር የለብንም።
ሁላችን እንደምናውቀው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ ወር በገባ በስድስት ኢየሱስ ተብሎ እንዳይጠራ ተደርጎ በአርሴማ በመተካቱ አዲሱ ትውልድ ኢየሱስን ሳይሆን አርሴማን በዕለቱ እያከበረ እንዲውል ተደርጓል።ቀደምት ኦርቶዶክሳውያን አባቶች ግን ይህንን ዕለት ኢየሱስ ብለው ሲሰይሙ በምክንያት ነው።በዕለቱ ከሌሎች ቀናት በተለየ ሁኔታ የኢየሱስን ክብር፣ የኢየሱስን አዳኝነት፣ከኢየሱስ ጋር በመሆን የሚገኘውን ጽቅና በረከት በሰፊው እንዲሰበክበት፣ስለ ኢየሱስ በሰፊው እንዲዘመርበት ነበር ፤ አለመታደል ሆኖ ግን የእነዚህ ዓይናማ ሊቃውንት ሥርዓት ተጥሶ እየተፈጸመ ያለው አዲስና እንግዳ ልማድ ሕዝቡ ኢየሱስን ከራሱ ቤት ይልቅ በሌሎች ድንኳን እንዲፈልገው እየገፋው ይገኛል።አንድ ጅል የተከለውን ሰባት ብልህ አይነቅለውም የሚባለው እንደዚህ ዓይነቱ ነውና ቅዱስ ሲኖዶስና ጠቅላይ ቤተክህነት በዚህ ጉዳይ በጥልቀት ሊያስቡበትና ሊያስተካክሉት ይገባል ግዴለሽነት የምንደኛ እረኛ ጠባይ ነው።
አሁን አሁንማ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ በገንዘብ ፍቅር ዓይናቸው የታወረ ካህናት ኢየሱስን በዕለቱ ከማሰብና በስሙ መቅደሱን ከመትከል ይልቅ ሕዝብ ሊስብልን የሚችለው የትኛው ነው በሚል ሥጋዊ አስተሳሰብ ላይ ብቻ ሲራኮቱ እያየን ነው።በዚህ ድርጊታችሁ ትውልዱን ወደ ሌላ ቤተእምነት ትገፋታላችሁ እንጂ ሌላውን ወደ ኦርቶዶክስ ማምጣት ፈጽሞ አትችሉምና ከገንዘብ ይልቅ ትውልዱን በክርስቶስ ፍቅር ነፍሱን እንዴት ማዳን እንደምትችሉ አትኩራችሁ ሰፊ ሥራ ሥሩ።
" ሁሉ በአግባብና በሥርዓት ይሁን ።" 1ቆሮ14፥40
መ/ር ታሪኩ አበራ
ለሌሎችም ሼር አድርጉት
Click here to claim your Sponsored Listing.