Orthodoxy

Orthodoxy

Share

Photos from Yohannes Eshetu's post 11/05/2020
23/02/2020

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን
የካቲት 16-ጌታችን ካረገ በኋላ በዚኽች ዕለት አምላክን በድንግልና የወለደች ክብርት እመቤታችን እንደጸለየችና ከተወደደ ልጇ የማይታበል የምሕረት ቃልኪዳን እንደተቀበለች የሚናገር ተአምር ይህ ነው፡- በዚህች ዕለት የክርስቲያን ወገኖች ሁሉ አምላክን ለወለደች ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ታላቅ በዓልን ያደርጋሉ፡፡ መታሰቢያዋን ለሚያደርግ፣ ስሟን ለሚጠራ፣ ለድኆችና ለችግረኞች እስከ ቀዝቃዛ ውኃ ድረስ ለሚሰጥ የክብር ባለቤት ከሆነ ልጇ ከመድኃኔዓለም ክርስቶስ ቃልኪዳን ተቀብላለችና፡፡ ይኽችም የከበረች እመቤታችን ተወዳጅ ልጇ ንጹሕ ሥጋዋን ተዋሕዶ ከብቻዋ ከኃጢአት በቀር የሰውነትን ሥራ ፈጽሞ ስለእኛ መዳን ወዶና ፈቅዶ ያደረገውን መከራ ተቀብሎ ሙቶ ተነሥቶ ካረገና በአባቱ ዕሪና ከተቀመጠ በኋላ እርሷን ክብርት እናቱን ድንግል ማርያምን በደቀመዝሙሩ በዮሐንስ ዘንድ ትቷት ነበር፡፡ ‹‹እነሆ ልጅሽ፣ እነኋት እናትህ›› ብሎ በአደራ እንዳስጠበቀው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምራ እመቤታችን ትጸልይ ዘንድ ያለማቋረጥ ወደ ልጇ መቃብር ሁልጊዜ ስትሄድ ኖረች፡፡ ይኸውም ጎልጎታ ነው፡፡ ክፉዎች አይሁድም በአዩዋት ጊዜ ቁጣንና ቅናትን ተመልተው በድንጋይ ሊወግሯትና ሊገድሏት ወደዱ፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ከዐይናቸው ሠወራት፡፡ እንዳትጸልይም ተማክረው ከልጇ መቃብር ዘንድ ጠባቂዎችን አኖሩ፡፡ እርሷ ግን በየለቱ መሄድን አላቋረጠችም ነበር፡፡ ጠባቂዎቹም አያዩዋትም-የልጇ የጌትነቱ መጋረጃ ሠውሯታልና፡፡ ቅዱሳን መላእክትም መጥተው ያገለግሏታል፤ ጌታችንም ዘወትር ይጎበኛታል የምትሻውንም ሁሉ ይፈጽምላት ነበር፡፡
ከዚህም በኋላ ቅዱሳን መላእክት እመቤታችንን ወደ ሰማያት አሳረጓትና የጻድቃንን ማደሪያዎች ሁሉ አሳዩዋት፡፡ አብርሃም ይስሐቅ ያዕቆብ ወዳሉበት አደረሷት፡፡ ከአዳም ጀምሮ እስከዚያች ዕለት ድረስ በአካለ ነፍስ ያሉ ቅዱሳን አባቶች ሁሉ ‹‹አንቺን ከሥጋችን ሥጋን፣ ከዐፅማችን ዐፅምን ለፈጠረልን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን! የአምላክ ልጅ ከአንቺ ሰው በመሆኑ በአንቺ ድኅነትን አግኝተናልና ከጥፋትም የሕይወት ወደብ ሆነሽናልና…›› እያሉ ሰገዱላት፡፡ ከዚያም ወደተወደደ ልጇ የእሳት መጋረጃ ወደተተከለበት ወደጌትነቱ ዙፋን አደረሷት፡፡ ጌታችንም እጇን ይዞ ወደ ውስጠኛው መጋረጃ አስገብቶ ከጌትነቱ ዙፋን ላይ አውጥቶ ከእርሱ ጋር አስቀመጣት፡፡ ያዘጋጀላትንም ዐይን ያላየው ጆሮ ያልሰማው በሰው ልቡና ያልታሰበ ተድላ ደስታን ሁሉ ነገራት፡፡ ከጌትነቱ ዙፋንም በታች የእስራኤል ንጉሥ አባቷ ዳዊትን የነቢያትና የመላእክት ማኅበር እንደግድግዳ ከበውት በመሰንቆ ሲያመሰግን አየችው፡፡ እንዲህም ይላል ‹‹ልጄ ስሚ በጆሮሽም አድምጪ፣ ወገንሽን የአባትሽንም ወገን እርሺ ንጉሥ ደም ግባትሽን ወዷልና እርሱም ጌታሽ ነውና፡፡››
ዳግመኛም የሥቃይን ቦታ ያሳዩዋት ዘንድ መላእክት ከዚያ ወሰዷት፡፡ ለሰይጣንና ለሠራዊቱ በእርሱ ጎዳና ለሚጓዙ ሁሉ ወደተዘጋጀ ወደጨለማው ዳርቻ አደረሷት፡፡ እመቤታችንም ማርያምም ‹‹ወዮልኝ ወደዚህ እንዳይመጡ ለሰው ልጆች ሁሉ ማን በነገራቸው!›› አለች፡፡ መልአኩም ‹‹እመቤቴ ቡርክት ማርያም ሆይ! ለአንቺም ከአንቺ በኋላም በቃልኪዳንሽ ለሚታመኑ እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ይኖራልና አትፍሪ›› አላት፡፡ ከዚህም በኋላ ወደቦታዋ መለሳት፡፡
ከዚያን ጊዜ ጀምራ እመቤታችን ስለኃጥአን እጅግ እያዘነች ኖረች፡፡ እንደዛሬጥቱም የካቲት 16 ቀን በጎልጎታ በተወዳጅ ልጇ የመቃብር ቦታ ቆማ ወደልጇ ስለኃጥአን ለመነች፡፡ የብርሃን እናቱ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በየካቲት ወር በ16ኛው ቀን በጎልጎታ በጸለየች ጊዜ እነሆ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወረደ፡፡ ከእርሱም ጋራ አእላፋት መላእክት አሉ፡፡ በዙሪያውም ሆነው ያመሰግኑታል፡፡ እርሱም ‹‹የወለድሽኝ እናቴ ማርያም ሆይ! ምን ላድርግልሽ?›› አላት፡፡ ክብርት እመቤታችንም ለተወደደ ልጇ እንዲህ ብላ መለሰችለት፡- ‹‹ልጄ ወዳጄ ሆይ! ጌታዬና ፈጣሪዬ አለኝታዬና መጠጊያዬ በእናቴም ማኅጸን ሳለሁ በአንተ ጸናሁ፣ አንተም ጠበቅኸኝ፣ ሁልጊዜ ስም አጠራሬ አንተ ነህ፡፡ አሁንም ጸሎቴንና ልመናዬን ስማኝ፣ ቃሌንም አድምጥ፡፡ እኔ እናትህ እኔም አገልጋይህ የምለምንህ ይህ ነው-መታሰቢያን ለሚያደርጉ፣ በስሜ አብያተ ክርስቲያናትን ለሚሠሩ ወይም የተራቆተውን ለሚያለብሱ፣ የተራበውን ለሚያጠግቡ፣ የተጠማውን ለሚያጠጡ፣ የታመመውን ለሚጎበኙ፣ ያዘነውን ለሚያረጋጉ፣ የተካውን ደስ ለሚያሰኙ ወይም ምስጋናዬን ለሚጽፉ፣ ልጆቹንም በስሜ ለሚሰይም፣ በበዓሌም ቀን በማኅሌት ለሚያመሰግን አቤቱ ዐይን ያላየውን፣ ጆሮ ያልሰማውን በሰውም ልቡና ያልታሰበውን በጎ ዋጋ ስጣቸው፡፡ በአማላጅነቴም የሚታመነውን ሁሉ ከሲኦል ነጻ አድርገው፡፡ ከአንተ ጋራ የደረሰብኝን ረኀቡንና ጥማቱን መከራውን ሁሉ አስብ›› አለችው፡፡ ተወዳጅ ልጇ መድኃኔዓለም ክርስቶስም ‹‹ወላጅ እናቴ ሆይ! እንዳልሽው እንደወደድሽ ይሁንልሽ፡፡ ጣፋጭቱ ከመዓር ከሸንኮር የሚጥመው ንጹሕነቱ ከኤዶም ምንጭ ውኃ ንጣቱ ከበረዶና ከወተት የበለጠውን ወተት መግበው ባሳደጉኝ ጡቶችሽ ቃልኪዳን ገባሁልሽ፡፡ ትእዛዜንና ሕጌን ባስተማሩ ዓስራ አምስቱ ነብያት፣ ሄሮድስ ባስገደላቸው ዓስራ አራት እልፍ የቤተልሔም ሕፃናት ቃልኪዳን ገባሁልሽ፡፡ የወንጌልን መንግሥት ለዓለም በሰበኩ ሐዋርያት፣ ስለእኔ ነፍሳቸውን ለሞት አሳልፈው ስለሰጡ ሰባ ሁለቱ አርድእት ቃልኪዳን ገባሁልሽ፡፡ ዙፋኔ በተዘጋጀባት ሉዓላዊት ሰማይ፣ የእግሬ መረገጫ በሆነች ታህታዊት ምድር ቃልኪዳን ገባሁልሽ፡፡ ነደ እሳት በሆነ የእሳት ነጋረጃዬ ፍጹም ማደሪያዬ በሆነ በአርያም ሰማይ ቃል ቃልኪዳን ገባሁልሽ፡፡ በተሰቀልኩበት ዕፀ መስቀል፣ እጅና እግሬ በተቸነከረበት ቅኖት ችንካር፣ በጦር በተወጋው ጎኔ ቃልኪዳን ገባሁልሽ፡፡ በዕለተ ዓርብ በፈሰሰው ደሜ በሕመሜና በሞቴ፣ ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊትም በከርሰ መቃብር ባደርኩበት ቃልኪዳን ገባሁልሽ፡፡ ከመቃብር ወጥቼ አዳምን ከነልጆቹ ከሲኦል ለማውጣት ወደሲኦል በመውረዴ በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተለይቼ ሙስናን መቃብርን አጥፍቼ በመነሳቴ፣ በዐርባኛው ቀን ወደ ሰማይ በማረጌ ዳግመኛም ዓለምን ለማሳለፍ በታላቅ ምስጋና በምመጣበት ቃልኪዳን ገባሁልሽ፡፡ ክቡር በሆነ ደሜ ቅዱስ በሆነ ሥጋዬ ቃልኪዳን ገባሁልሽ፡፡ ብርክት እናቴ ድንግል ማርያም ሆይ! የሰጠሁሽም ቃልኪዳን እንዳይታበል አማንዬ ብዬ በራሴ ማልኩልሽ›› አላት፡፡
አምላክን በድንግልና የወለደች ክብርት እመቤታችን ከቃልኪዳኗ በረከት ትክፈለን!
ለመረጣት ለእግዚአብሔር አብ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷም ነፍስ ነስቶ ለተዋሐዳት ለእግዚአብሔር ወልድ ለአጸናት ለእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይሁን! አሜን!!!
+ + +
ዳግመኛም በዚህች ዕለት የካቲት 16 ቀን
+ የመጥምቀ መለኮት የቅዱስ ዮሐንስ እናት የከበረች ቅድስት ኤልሳቤጥ ዕረፍቷ ነው፡፡
+ የሚዳው ጻድቁ አቡነ መልከጼዴቅ ልደታቸው ነው፡፡
+ የላሊበላ ታላቅ ወንድም የሆነው የላስታው ጻዲቁ ንጉሥ ቅዱስ ገብረ ማርያም ዕረፍቱ ነው፡፡
+ ዳግመኛም በዚህች ዕለት ጌታችንን ድንቅ ነገር በመለመኑ ፈቃዱን የፈጸመለት ጻድቁ ንጉሥ ቅዱስ ነዓኩቶ ለአብና ልጁ ታስበው ይውላሉ፡፡
ቅድስት ኤልሳቤጥ፡- ይኽችም ቅድስት ከኢየሩሳሌም የሆነች የእናቷ ስም ሶፍያ ነው፡፡ እርሷም ከሌዊ ነገድ ከአሮን ወገን ለሆነ ለማጣት ልጁ ናት፡፡ በዝምድና አምላክን ለወለደች ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም የእናቷ እኅት ልጅ ናት-ማጣት ሦስት ልጆችን ወልዷልና፡፡ የታላቂቱ ስም ማርያም ነው፡፡ እርሷም ወደ ግብፅ በተሰደደች ጊዜ እመቤታችንን ያገለገለቻት ሰሎሜን ወለደቻት፡፡ ሁለተኛዋም ሶፍያ ናት፡፡ እርሷም የዚኽች የቅድስት ኤልሳቤጥ እናቷ ናት፡፡ የታናሽቱም ስም ሐና ነው፡፡ እርሷም ክብርት እመቤታችንን ድንግል ማርያምን ወለደቻት፡፡ በመሆኑም ሰሎሜ፣ ኤልሳቤጥና እመቤታችን ድንግል ማርያም የእኅትማማቾች ልጆች ናቸው፡፡
ይኽችንም ቅድስት ኤልሳቤጥን ደገኛው ካህን ዘካርያስ አገባት፡፡ የከበረ ቅዱስ ወንጌልም ስለእነርሱ ሲመስክር ‹‹በይሁዳ ንጉሥ በሄሮድስ ዘመን ከአብያ ክፍል የሆነ ዘካርያስ የሚባል አንድ ካህን ነበረ፤ ሚስቱም ከአሮን ልጆች ነበረች፥ ስሟም ኤልሳቤጥ ነበረ። ሁለቱም በጌታ ትእዛዝና ሕግጋት ሁሉ ያለ ነቀፋ እየሄዱ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ›› ብሏል፡፡ ሉቃ 1፡5-6፡፡
ቅድስት ኤልሳቤጥም መካን ስለሆነች ካህኑ ዘካርያስና እርሷ ወደ እግዚአብሔር የሚለምኑና የሚማልዱ ሆኑ፡፡ አርጅተውም የመውለጃቸው ዘመን ባለፈ ጊዜ እግዚአብሔር የራማውን ልዑል ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤልን ወደ ዘካርያስ ልኮ ጸሎታቸው ልመናቸው እንደተሰማ ስለ መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስም መወለድ ከእርሱ ስለሚሆነው ነገረው፡፡ ከዚህም በኋላ ቅድስት ኤልሳቤጥ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስን ፀንሳ ወለደቸው፡፡ ከሰዎችም የሚደርስባት ሽሙጥ ተወግዶላት እጅግ ደስ አላት፡፡ የአካባቢዋ ሰዎችም ሁሉ መካን በመሆኗ ቅድስት አልሳቤጥን ‹‹ጡተ ደረቅ፣ ማኅፀንሽም የተዘጋ፣ በረከትን ያጣሽ፣ መርገምንም የተመላሽ፣ የበቅሎ ዘመድ፣ ቢወልዷት እንጂ አትወልድ…›› እያሉ ይሰድቧት ነበር፡፡ ቅድስት አልሳቤጥም በዚህ ወራት መፀነሷን ባወቀች ጊዜ ‹‹ስድቤን ሁሉ ከሰው ያርቅልኝ ዘንድ እግዚአብሔር በረድኤት በጎበኘኝ ጊዜ እንዲህ አደረገኝን!›› ብላ አምስት ወር ፅንሷን ሠወረች፡፡ ለማንም አልተናገረችም፡፡ ምክንያቱም ይሰድቧት የነበሩት ክፉዎች ‹‹ይህቺ ሴት የበላችው ቂጣ ቢነፋት ፀነስኩ ትላለች›› ብለው ቢሰድቧት እንጂ ሌላ ረብ ጥቅም ባልነበረው ነበር፡፡ ኤልሳቤጥም ስድስት ወር በሆናት ጊዜ መልአኩ ለቅድስት ድንግል ማርያም አምላክን እንደምትወልድ አበሰራት፡፡ ድንግል ማርያምም መልአኩ ስለ ኤልሳቤጥ መፀነስ የነገራትን ለማረጋገጥ ወደ እርሷ ሄደች፡፡ እመቤታችንም ‹‹እንዴት ነሽ?›› ስትላት በኤልሳቤጥ ላይ መንፈስ ቅዱስ አደረባት፡፡ ድንፁዋንም በሰማች ጊዜ በማኅፀኗ ያለው ፅንስ በደስታ ሰገደ፡፡
ርጉም የሆነ ሄሮድስ መሢሕ ሕፃን ክርስቶስ መወለዱን ሲሰማ መንግሥቴን ይቀማኛል ብሎ በመፍራት በቤቴልሔም ያሉ ሁለት ዓመትና ከዚያ በታች ያሉ 144,000 (መቶ ዐርባ አራት ሺህ) የቤቴልሔም ሕፃናትን በሰይፍ ሲያስገድል ድንግል ማርያም ከልጇ ጋር ወደ ግብፅ ስትሰደድ፣ ቅድስት ኤልሳቤጥ ደግሞ ወደ ሲና በረሃ ሄዳ ልጇን ዮሐንስን ከዚያ ደብቃዋለች፡፡ ከመሄዷ በፊት ግን ከባሏ ከዘካርያስ ጋር ሲሰነባበቱ የሚሆነውንም ሁሉ እርሱ ቀድሞ ያውቅ ነበርና ‹‹ሕፃኑን ልጄን ሲያጡ እኔን ይገድሉኛል፣ አንቺ ግን ወደ በረሃው ይዘሽው ሂጂና በዚያ ሸሽጊው›› ብሎ መክሯታል፡፡ እርሷም ከሄደች በኋላ የርጉም ሄሮድስ ጭፍሮች ዮሐንስን ባጡት ጊዜ ወደ ዘካርያስ መጥተው ‹‹ልጅህን ወዴት አድርሰኸው ነው? ወዴትስ ደበቅኸው? አሁን ከደበቅህበት አምጥተህ ፈጥነህ አስረክበን›› በማለት የፍጥኝ አስረው ካሠቃዩት በኋላ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ከሚሠዋበት በቤተ መቅደስና በዕቃ ቤት መካከል አንገቱን ቆርጠው ገደሉት፡፡ የዘካርያስም ደም እስከ ሰባት ዓመት ድረስ እየፈላ ደሙ ሲካሰሳቸው ኖረ፡፡
ቅድስት ኤልሳቤጥም ልጇን ዮሐንስን ይዛ ወደ በረሃ ከገቡ አምስት ዓመት በሆናቸው ጊዜ ቅዱስ ዮሐንስ ዕድሜው ሰባት ዓመት ከመንፈቅ ከሆነው በኋላ እናቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ ዐረፈች፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም በሰፊዋ በረሃ ውስጥ በአራዊቶች መካክል ብቻውን ቀረ፡፡ ለዮሐንስ ግን በእርሱ ላይ ምንም መጥፎ ነገር ሳያደርጉ የቶራና የአንበሳ የነብርም ልጆች እንደ ወንድምና እንደ እኅት ሆኑት፡፡ አራዊቶችም ሁሉ ወዳጅ ሆኑት፡፡ ምግቡም የበረሃ ቅጠል ነው፤ መጠጡም ከተቀመጠባት ድንጋይ ሥር የፈለቀችለት ውኃ ነበረች፡፡ ዮሐንስ ሰውነትን አለምልመው፣ ሥጋን አለስልሰው፣ ገጽንና ፊትን የሚያሳምሩትን ምግቦች አልተመገበም፡፡ የበረሃ ቅጠሎችንም አልተመገበም፡፡
ንጉሥ ሄሮድስ በሞተ ጊዜ እነሆ የእግዚአብሔር መልአክ በግብፅ አገር ለዮሴፍ በሕልም ተገልጦ በመታየት ‹‹እነሆ የዚህን ሕፃን ነፍስ የሚሹ ሙተዋልና ተነሥተህ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ምድረ እስራኤል ተመለስ›› ካለው በኋላ የ86 ዓመቱ አረጋዊው ዮሴፍ ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን ይዞ ወደ ምድረ እስራኤል ገባ፡፡ ጌታችን ‹‹ልጄ ናዝራዊ ይባላል›› ተብሎ በነቢይ የተነገረው ቃል ይደርስ ይፈጸም ዘንድ መጥቶ ናዝሬት በምትባል አገር ተቀመጠ፡፡ ለሞት ይፈልገው የነበረው የተረገመ ከሃዲ ሄሮድስ ከሞተ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ ከድንግል ማርያም ጋር ከምድረ ግብፅ ተመልሶ በናዝሬት ተቀምጦ ሳለ እነሆ የዕድሜ ባለፀጋ የሆነችው የዮሐንስ እናት ክብርት ኤልሳቤጥ ልጇን ዮሐንስን ይዛው ወደ ደብረሲና በረሃ ከገቡ ከአምስት ዓመት በኋላ ዐረፈች፡፡ ዮሐንስም በእናቱ አስክሬን አጠገብ ተቀምጦ በእጅጉ እያዘነ መሪር ልቅሶንም እያለቀሰ ሳለ የተሸሸገውን ሁሉ የሚያውቅ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በናዝሬት ተቀምጦ ሳለ የኤልሳቤጥን መሞት፣ እናቱም ስለሞተችበት ዮሐንስ ብቻውን ከበረሃ ውስጥ ተቀምጦ እያለቀሰ መሆኑን ዐወቀ፡፡ ጌታችን በናዝሬት ተቀምጦ ሳለ የቅድስት ኤልሳቤጥን መሞትና የወዳጁ ዮሐንስ ኃዘንና ማልቀስ ባወቀ ጊዜ እርሱም በናዝሬት ሆኖ ያለቅስ ጀመር፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ልጇ ወዳጇ ሲያለቅስ ባየችው ጊዜ ‹‹ልጄ ወዳጄ ሆይ! ምን ሆንክ? ስለምንስ ታለቅሳለህ?›› ብላ ጠየቀችው፡፡ ጌታችንም ለቅድስት እናቱ እንዲህ በማለት መለሰላት፡- ‹‹እነሆ ወገንሽ የሆነችው ኤልሳቤጥ ዐረፈች፤ ዮሐንስንም ብቻውን ከበረሃ ውስጥ ተወችው፡፡ ዮሐንስም ሕፃን ስለሆነ የሚያደርገውን አጥቶ በእናቱ አስክሬን አጠገብ ከፊት ለፊቷ ተቀምጦ በመረረ ኃዘን ያለቅሳል፡፡ እናቴ ሆይ እኔም ዘመድሽ የሆነ የዮሐንስን ልቆሶ ስላወቅሁኝና የእርሱም ኃዘን ስለተሰማኝ የማለቅሰው ስለዚህ ነው›› አላት፡፡ በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የፀናች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም የኤልሳቤጥን መሞት በሰማች ጊዜ በጣም ምርር ብላ አለቀሰች፡፡ ያንጊዜም ብርሕት ደመና መጥታ ከፊታቸው ቆመች፤ ፈጥናም ተሸከመቻቸውና ኤልሳቤጥ ከሞተችበት ዮሐንስም ካለበት ቦታ ከደብረሲና በረሃ ውስጥ ወስዳ አደረሰቻቸው፡፡ ዮሐንስም ባያቸው ጊዜ ደነገጠ፡፡ ከዚያ በፊት ሰው አይቶ ስለማያውቅ የእናቱን አስክሬን ብቻውን ትቶ ወደ ጫካ ሸሸ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የዮሐንስን ፍርሃት አራቀለትና እንዲህ አለው፡- ‹‹እኛን ከማየትህ የተነሣ አትፍራ፣ አትደንግጥም፤ አይዞህ እነሆ የእናትህ ዘመዶች ማርያምና ሰሎሜ በእናትህ አስክሬን ላይ መልካም ነገር ሊያደርጉ መጥተዋልና ና ወደ እኛ ቅረብ›› አለው፡፡ ዮሐንስም ይህን ቃል ከጌታችን አንደበት በሰማ ጊዜ ወደኋላው ተመለሰ፡፡ ከመሬትም ላይ ወድቆ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ሰገደለት፡፡
ጌታችንም እመቤታችን ማርያምንና ሰሎሜን ‹‹በጠማው ጊዜ ለእርሷ ይጠጣ ዘንድ ለዮሐንስ በፈለቀችለት ውኃ የኤልሳቤጥን ሥጋ አጥባችሁ ገንዙ›› አላቸው፡፡ እንዳዘዛቸውም የኤልሳቤጥን አስክሬን አጥበው ገነዙ፡፡ ጌታችንም ቅዱስ ሚካኤልንና ቅዱስ ገብርኤልን ይመጡ ዘንድ አዘዛቸው፡፡ እነርሱም ፈጥነው እንደ ዐይን ጥቅሻ ከሰማይ ወርደው መጡና ከጌታችን ፊት ቆሙ፡፡ ጌታችንም ‹‹የኤልሳቤጥን ሥጋ የሚቀበርበትን መሬት ቆፍሩ›› አላቸው፡፡ ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤልም መቃብሩን ይቆፍሩ ዘንድ ጀመሩ፡፡ ጌታችን ዘካርያስንና ስምዖንን በአካለ ነፍስ ከሰማይ መጥተው በኤልሳቤጥ አስክሬን ላይ ጸሎተ ፍትሃቱን ያደርሱ ዘንድ አዘዛቸው፡፡ እነርሱም የኤልሳቤጥ አስክሬን ካለበት ቦታ ላይ ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል፣ እመቤታችን ማርያምና ሰሎሜ ከጌታችን ፊት ቆመው ሳለ ስምዖንና ዘካርያስ በአስክሬኑ አጠገብ ቆመው ጸሎተ ፍትሃቱን ያደርሱ ጀመር፡፡ ጸሎተ ፍትሃቱንም በጨረሱ ጊዜ መላእክት በቆፈሩት መቃብር ውስጥ ቀበሩዋትና የስምዖንና የዘካርያስ ነፍስ ወደነበረችበት ቦታዋ ተመለሰች፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የኤልሳቤጥን መቃብር በትእምርተ መስቀል አምሳል ደፈነው፡፡ ኤልሳቤጥም ያረፈችበት ዕለት የካቲት ዓሥራ ስድስት ቀን ነው፡፡
ከዚህ በኋላ ዮሐንስን ብቻውን ከበረሃ ውስጥ ትተውት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ጋር ወደ ናዝሬት ለመመለስ ከደመናዋ ላይ ተሣፍሮ ተነሣ፡፡ ያንጊዜም ክብርት እመቤታችን ልጇን እንዲህ አለችው፡- ‹‹ጌታዬና አምላኬ ፈጣሪዬ ሆይ! ስለምን ዮሐንስን ብቻውን ከበረሃ ውስጥ ትተወዋለህ? እንዴትስ ትተነው እንሄዳለን? ወደዚህ ቦታ ይዛው የሸሸችው እናቱ ጥላው ሞታ በመቃብር ውስጥ ተቀብራለች ከእኛ ጋር ይዘነው እንሂድ እንጂ›› አለችው፡፡ ዳግመኛም እመቤታችን እንዲህ አለችው፡- ‹‹ነፍስ ያለወቀ ሕፃን ስላሆነ አራዊት ይበሉታልና ይዘነው መሄድ አለብን›› አለችው፡፡ ጌታችንም ለቅድስት እናቱ እንዲህ በማለት መለሰላት፡- ‹‹በመምህርነት ወጥቶ ለእስራኤል ታይቶ እስከሚያስተምር ድረስ የሰማያዊው አባቴ ፈቃድ በበረሃ ውስጥ ብቻውን እንዲኖር ነው፡፡ አንቺ ብቻውን እንዴት ከበረሃ ይኖራል ትያለሽ፤ አራዊቶች እንዳይጣሉት ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ከእርሱ አይለይም፡፡ በፈለገው ነገር ሁሉ እንዲራዱትና እንዲታዘዙለት መላእክተ ብርሃንን አዝለታለሁ፡፡ ብርሃናዊው መልአክ ገብርኤልም ሰማያዊ ኅብስትን ለምግቡ ያመጣለታል፤ በጠማውም ጊዜ እንደ ወተት የነጣችውን እንደ ወለላ ማርም የጣፈጠችውን ውኃ ከኤዶም ገነት ያመጣለታል፡፡ ይህችንም እርሱ ካለበት ድንጋይ ሥር የምትፈልቀውን ውኃ እንደ እናቱ ጡት ለአፉ የጣፈጠች አደርግለታለሁ፡፡ አንቺ ብቻውን እንዴት በበረሃ ውስጥ ይኖራል ትያለሽ እስከ ዛሬ ድረስም የጠበቅሁት እኔ ነኝ፣ ሌላ ማን ጠበቀው ብለሽ ነው? እኔ አይደለሁምን? ወዳጄ ዮሐንስን ሰማያዊው አባቴ ከዚህ ዓለም ፍጥረት ሁሉ በጣም አብልጦ ይወደዋል፡፡ አባቱ ዘካርያስም በሥጋው ቢሞት በነፍሱ ሕያው ስለሆነ ዮሐንስን ለማጽናናት በአካለ ነፍስ ከእርሱ እንዳይለየው አደርጋለሁ፡፡ እናቱ አልሳቤጥም በሥጋዋ ብትሞት በነፍሷ ሕያዊት ስለሆነች ታጽናናው ዘንድ በነፍሷ በፍጹም ከእርሱ እንዳትለየው አደርጋለሁ፡፡ ዮሐንስን የተሸከመች ማኅፀን ንዕድ፣ ክብርት ስለሆነች በሥጋዋ ውስጥ መጥፎ ሽታ ክፉ መዓዛ አይገኝባት፣ በመቃብሯም ውስጥ ትሎች አይገኙበት፡፡ ድንግል እናቴ ሆይ! አንቺ እኔን ፀንሰሽ ሳለሽ ወደ ኤልሳቤጥ በሄድሽ ጊዜ በእጇ ይዛ ጨብጣ፣ በአፏ በሳመችሽ ጊዜ እንዲህ ብላ ትንቢት ተናግራለች፡፡ ‹‹አንቺ ከሴቶች ሁሉ ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ፤ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው፤ የጌታዬ እናቱ ወደ እኔ ትመጪ ዘንድ እኔ ምንድነኝ? ከእግዚአብሔር አግኝተው የነገሩሽን ቃል ይደረጋል ብለሽ የተቀበልሽ አንቺ ብፅዕት ነሽ፣ ክብርት ነሽ› ብላ ስላመሰገነችሽ እንኳን ሥጋዋ ሊፈርስ ይቅርና መግነዟም አይለወጥም፤ መቃብሯም አይጠፋም፤ ነፍሷንም ከሥጋዋ ጋር እንድትኖር አደርጋታለሁ፡፡›› ይህን የመሰለ ነገር ስለ ወዳጁ ዮሐንስ ለድንግል እናቱ ነግሯት ከጨረሰ በኋላ ዮሐንስን ከበረሃ ውስጥ ትተውት በደመና ላይ ተጭነው ወደ ናዝሬት ተመለሱ፡፡
የቅድስት ኤልሳቤጥ ረድኤት በረከቷ ይደርብን በጸሎቷ ይማረን!
+ + +
ጻድቁ ንጉሥ ቅዱስ ነዓኵቶ ለአብ፡- የስሙ ትርጓሜ ‹‹እግዚብሔር አብን እናመስግነው›› ማለት ነው፡፡ የቅዱስ ላሊበላ የወንድም ልጅ ሲሆን ከ11ዱ የዛጉዌ ነገሥታት ውስጥ 10ኛው ነው፡፡ አባቱ ቅዱስ ገብረ ማርያም ሥልጣኑን ለወንድሙ ለቅዱስ ላሊበላ ትቶ በመመንኮስ በበዓት ተወስኖ በጾም በጸሎት ሲጋደል ጌታችን ተገልጾለት ‹‹ክብሩ እንደ መላእክት የሆነ ልጅ ትወልዳለህና ወደቤትህ ተመለስ›› ብሎ አዘዘው፡፡ ንጉሡ ገብረማርያምም ‹‹40 ዓመት ስነግሥ ያልወለድኩትን አሁን ዓለም በቃኝ ስል ትወልዳለህ የተባልኩት ልጅ ምን ዓይነት ልጅ ይሆን!›› እያለ ወደ ቤቱ ተመለሰ፡፡ ሚስቱን መርኬዛንም መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ካበሰራት በኋላ ነአኵቶለአብ ጌታችን በተወለደበት ዕለት ታኅሳስ 29 ቀን ተወለደ፡፡ ቅዱስ ላሊበላም ቀደም ብሎ የተወለደው እንዲሁ በጌታችን የልደት ቀን ታኅሳስ 29 ቀን 1101 ዓ.ም ነው፡፡
መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልም ነአኵቶለአብ እንደሚወለድ ቀድሞ ለንጉሥ ላሊበላ ነግሮት ነበርና አሁን ሲወለድ ‹‹ያ የነገርኩህ ሕፃን ተወልዷልና ወስደህ በሃይማኖት አንጸህ አሳድገው›› ብሎታል፡፡ እንዳለውም ሃይማኖቱን ጠንቅቆ እያስተማረ በእንክብካቤ አሳደገው፡፡ ግብፅ ሄዶ ከአቡነ ቄርሎስ ዲቁናን ተቀበለ፡፡ በኋላም ቅስናን ተቀበለ፡፡ ቅዱስ ላሊበላ ቤተ መቅደሶቹን ሠርቶ ከጨረሰ በኋላ በሕይወት ሳለ መንግሥቱን ስላወረሰው ከላሊበላ በኋላ ነግሦ ኢትዮጵያን መርቷል፡፡ ዕድሜው ሲደርስ መልአኩ ሚስት እንዲያጭለት ለቅዱስ ላሊበላ ነግሮት ሲያጭለት እግዚአብሔርን በድንግልና ማገልገል ይፈልግ ነበርና በዚህም እጅግ ሲያዝን እመቤታችን ተገልጻለት ጋብቻው ከእግዚአብሔር መሆኑን ነግራ አጽናንታዋለች፡፡ ‹‹የጌታህ ፈቃድ ነውና አትዘን ይልቁንም አግባ፣ ክብርህም ከደናግላን አያንስም›› ብላ ስለነገረችው ሚስት ቢያገባም ልክ እንደ ቅዱስ ዲሜጥሮስና ልዕልተወይን ንጽሕናቸውንና ድንግልናቸውን ለመጠበቅ በመማከር በግብር ሳይተዋወቁ ለ25 ዓመታት በድንግልና ሆነው በትዳር ኖረዋል፡፡ ምንኛ ድንቅ ነው የአባቶቻችን ጽናትና ተጋድሎ!!! እግዚአብሔርን በንጽሕና ለማገልገል ያላቸው ቁርጠኝነትስ በምን ቃላት ይገለጻል!!! ከዚህ በኋላ መልአክ መጥቶ ቅዱስ ነአኵቶለአብንና ባለቤቱን ‹‹በንጽሕና የተጋባችሁት ልትወልዱ ነው እንጂ ዝም ብላችሁ ልትኖሩ አይደለም›› አላቸው፡፡ እነርሱም በዚህ ጊዜ በጋብቻ 25 ዓመታት በድንግልና አብረው ከኖሩ በኋላ አንድ ቀን ብቻ በግብር ቢተዋወቁ እጅግ የሚያምርና የሚያሳሳ ወንድ ልጅ ወለዱ፡፡
ጻድቁን ንጉሥ ቅዱስ ነአኵቶለአብን ይበልጥ የምናደንቅበት ነገር የተፈጠረው ከዚህ በኋላ ነው፡፡ በመልአክ ትእዛዝ የወለደው ልጁ እጅግ የሚያምርና የሚያሳሳ ቢሆንም ንጉሡ ቅዱስ ነአኵቶለአብ ግን በእግዚአብሔር መንፈስ የወደፊቱን ያውቅ ነበርና ሱባኤ ገብቶ ‹‹በእኔ እግር ተተክቶ ሲነግሥ ፍርድ አጣሞ አንተንም ሰውንም ከሚበድል ይህን ልጄን ቅሰፍልኝና ሄሮድስ ካስፈጃቸው ሕፃናት ጋር ደምርልኝ›› በማለት ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፡፡ እንደጸሎቱም ጌታችን በዛሬዋ ዕለት የካቲት 16 ቀን ልጁን በሰላም አሳርፎለት ሄሮድስ ካስፈጃቸው ሕፃናት ጋር ደምሮለታል፡፡ በዚህም ጊዜ መኳንንቶቹ፣ መሳፍንቶቹና ሕዝቡ ሁሉ ለልቅሶ ቢመጡ እርሱ ግን በቤተ መንግስቱ በልቅሶ ፈንታ ታላቅ የደስታ ድግስ አድርጎ ስለጠበቃቸው ‹‹የንጉሡ ልጅ ሞተ የተባለው ውሸት ነው›› ብለዋል፡፡
ቅዱስ ነአኵቶለአብ ክህነትን ከንግስና ይዘው ኢትዮጵያን ከመሩ ከአራቱ የዛጉዌ ነገሥታት አንዱ ሲሆን በነገሠበት 40 ዓመት ሙሉ ዓርብ ዓርብ ቀን የክርስቶስን ሕማም እያሰበ በዕንቁና በወርቅ በተሸቆጠቆጠው ዘውዱ ፈንታ የእሾህ አክሊልን ደፍቶና በአምስቱ ቅንዋተ መስቀሎች ምሳሌ አምስት ጦር ዙሪያውን ተክሎ እያለቀሰ ይጸልይና ይሰግድ ነበር። ለፍርድም በተቀመጠ ጊዜ ከንግሥና ልብሱ ውስጥ በስውር ማቅ ለብሶና ሰውነቱን በሰንሰለት አስሮ ከላይ ግን በክብር ልብሱ ተሸፍኖና በወርቅ ወንበር ተቀምጦ ይፈርድ ነበር፡፡ ፍርድ ሲሰጥም ሁሉንም ነገር በመንፈስ ቅዱስ እያውቅ ነበር፡፡ ይህ ጻዲቅና ቅዱስ ንጉሥ በዘመኑ ግብፆች ግብር አንሰጥም ብለው ስላመፁበት የዓባይን ወንዞች በጸሎቱ ወደ ሌላ ቦታ እንዲፈሱ ስላደረገባቸው ግብፆች ከበፊቱ ጨምረው ግብራቸውን አምጥተው ሰጥተውት ግዝቱን አንስቶላቸዋል፡፡ የዚህ ጻድቅ ንጉሥ ረድኤት በረከቱ ይደርብን በጸሎቱ ይማረን!
+ + +
ጻድቁ ንጉሥ አቡነ ገብረ ማርያም፡- የላስታ ነገሥታት የዘር ሐረጋቸው ከንጉሥ ሰሎሞን ዘር ሲያያዝ የመጣ ነው፡፡ ከ10ኛው እስከ 13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን (920-1253 ዓ.ም ገደማ) በላስታ ቡግና ምድር የነገሡ የላስታ ቡግና ተወላጅ የሆኑ የኢትዮጵያ ቅዱሳን ነገሥታት የንግሥናቸው መጠሪያ ‹‹የዛጉዌ ሥርወ መንግሥት›› ወይም ‹‹የላስታ መንግሥት›› በመባል ይታወቃል፡፡ ከላስታ (ከዛጉዌ) ነገሥታት መካከል ቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ፣ ቅዱስ ገብረ ማርያም፣ ቅዱስ ላሊበላና ቅዱስ ነአኵቶ ለአብ እነዚህ አራቱ ነገሥታት እንደ መልከጼዴቅ (ዘፍ 14፡18) ክህነትን ከንግሥና፣ ቅድስናን ከንጽሕና ጋር አንድ አድርገው በመያዝ እግዚአብሔርንም ሰውንም በቅድስናና በንጽሕና አገልግለው አልፈዋል፡፡
ጻድቁ ንጉሥ ቅዱስ ገብረማርያም በሌላኛው ስማቸው ሐርቤይ እየተባሉ የሚጠሩ ሲሆን የቅዱስ ላሊበላ ታላቅ ወንድም ናቸው፡፡ ታላቁን ጻድቅ ንጉሥ ቅዱስ ነዓኵቶ ለአብን ወልደዋል፡፡ አባታቸው ዣን ስዩም 40 ዓመት ከነገሡ በኋላ በ76 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ ልጃቸው ገብረ ማርያም ንግሥናውን ተቀብለዋል፡፡ ከእርሳቸው ቀጥሎ ታናሽ ወንድማቸው ቅዱስ ላሊበላ ተወልዶ እንደሚነግስ በትንቢት ተነግሮ ነበር፡፡ ይህን ጊዜ ከላሊበላ ጋር በአባት እንጂ በእናት ይለያዩ ነበርና የበጎ ነገር ጠላት የሆነ ክፉ ሰይጣን የእኅታቸው ክፉ ምክር ተጠቅሞ በወንድማቸው በላሊበላ ላይ በቅናት ክፉ እንዲያስቡ አድርጓቸዋል፡፡ ስለ ንግሥናቸው ሲሉ ምንም እንኳን በወንድማቸው ላይ ክፉ አስበው የነበረና በእኅታቸውም ክፉ ምክር መርዝ የሰጡት ቢሆንም በኋላ በክፉ ሀሳባቸው እጅግ ተፀፅተው ‹‹አምላኬንም ወንድሜንም አሳዘንኩ›› በማለት ወንድማቸውን ይቅርታ በመጠየቅ ላሊበላን አንግሠውት እርሳቸው መንኩሰው ገዳም ገብተዋል፡፡
ቅዱስ ላሊበላ ካለበት አክሱም ድረስ ሄደው በዕንባና በልቅሶ ይቅርታ ጠይቀው ወደ ሀገራቸው ሮሐ ከተማ ይዘውት በመምጣት መንግሥታቸውን አስረክበውት ነው የመነኑት፡፡ በምንኩስናም ሆነው በታላቅ ተጋድሎ በጾም በጸሎት በመትጋት እግዚአብሔርን እያገለገሉ እያለ ጌታችን ተገልጦላቸው ‹‹ክብሩ እንደ መላእክት የሆነ ታላቅ ልጅ ትወልዳለህና ወደቤትህ ተመለስ›› ብሎ ከነገራቸው በኋላ ወደቤታቸው ተመልሰው ቅዱስ ነአኵቶ ለአብን ወልደዋል፡፡
ንጉሥ ቅዱስ ገብረ ማርያም በዘመናቸው ከነበሩት ከእስክንድሪያ ሊቀ ጳጳሳት ከአባ ዳንኤል ጋር መልእክት በመላላክ ‹‹ከሀገሬ ሊቃውንት መነኮሳት የሕዝቡን ቋንቋ የሚሰሙና የሚያስተምሩ ጳጳስ ይሹሙልን›› በማለት ለእስክንድሪያ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ምንም እንኳን የእስክንድሪያ ሲኖዶስ በወቅቱ ኢትዮጵያ የራሷን ልጆች እንድትሾም ስላልፈለጉና በወቅቱ ፈቃደ እግዚአብሔርም ስላልነበረ የቅዱስ ገብረ ማርያምን ጥያቄ ንግሥት ዘውዲቱና ዐፄ ኃይለሥላሴ ድጋሚ በመጠየቅ ፍጻሜውን እንዲያገኝ ቢያደርጉትም መሠረቱን ግን የጣሉት ዐፄ ገብረ ማርያም ናቸው፡፡ በዘመናቸው ብዙ አብያተ ክርስቲያናትንም ያሠሩ ሲሆን ጊዜ ዕረፍታቸው ሲደርስ ጌታችን ተገልጦላቸው ‹‹የእኔን መከራ እያሰብክ ከዓይንህ ዕንባ ሳያቋርጥ በጾም በጸሎት ተወስነህ ስላገለገልኸኝ በአንተ ስም ለተራበ ያበላውን፣ ለተጠማ ያጠጣውን፣ ለታረዘ ያለበሰውን ምሬልሃለሁ›› በማለት ትልቅ ቃልኪዳን ሰጥቷቸው በካቲት 16 ቀን በታላቅ ክብር ዐርፈዋል፡፡ ጻድቁን ንጉሥ ዐፄ ገብረ ማርያምን ሚያዝያ 10 ቀን የሚነበበው ስንክሳር በሰፊው ይጠቅሳቸዋል፡፡ረድኤት በረከታቸው ይደርብን በጸሎታቸው ይማረን!
+ + +
ዳግመኛም በዚህች ዕለት ጻድቁ አቡነ መልከጼዴቅ ዘሚዳ ልደታቸው ነው፡፡ (የዕረፍታቸውን ዕለት ግንቦት አራትን ይመለከቷል)
ኢትዮጵያዊው ጻድቅ አቡነ መልከጼዴቅ፡- አቡነ መልከጼዴቅ በ13ኘው መ/ክ/ዘ መጨረሻ በንጉሥ ዐፄ በእደ ማርያም ዘመነ መንግሥት የነበሩ እደጃቸው የተቀበረውን ሰው አፈር የማያስበሉ እጅግ ድንቅ ቃል ኪዳን ያላቸው ታላቅ አባት ናቸው፡፡ የአምላካቸውን የክርስቶስን መከራ ለማሰብ ገዳመ ቆሮንቶስን የመሰለ ዋሻ ቆፍረውና በዚያ ገብተው ቀንና ሌሊት ዘግተው በረደኝ ፀሐይ ልሙቅ፣ ጨለመኝ ብርሃን ልይ ሳይሉ በጸሎት ብቻ ዘግተው በመኖር ራሳቸውን በችንካር እያቆሰሉና ጭንቅላታቸውን እያተሉ ትሉን ለሰማይ አእዋፍ ይመግቡ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ወልድ የተገረፈውን ግርፋት እያሰቡ በየቀኑ እስከ 3ሺህ ድረስ ይሰግዱ ሰውነታቸውንም እንዲሁ ይገርፉ እንደነበር መጽሐፈ ገድላቸው ይናገራል፡፡ የክርስቶስን መቸንከር እያሰቡ እጅና እግራቸውን፣ ወገብና ደረታቸውን በብረት ቸንክረው መከራውን ያስቡ ነበር፡፡ ጎኑ በጦር መወጋቱን አስበው አጥንታቸው እስኪሰበር ድረስ ጎናቸውን ወጉ፡፡ ሐሞትና ከርቤ መጠጣቱን አስበው እርሳቸውም መራራ ይጠጡና አንክርዳድን ይመገቡ ነበር፡፡ ሞቱን አስበው ደም እንባን ያነቡ ነበር፡፡ በእንደዚህ ዓይነቱ ተጋድሎ የክርስቶስን መከራ እያሰቡ ነቢያን፣ ሐዋርያትን፣ ሰማዕታትን፣ ደናግል መነኮሳትን መስለው ሁሉን እያከናወኑ እያለ የወዳጆቹን መከራ የማይዘነጋ፣ የሰውን የድካሙን ዋጋ ፈጽሞ የማያስቀር አምላክ ሠራዊተ መላእክትን አስከትሎ መጥቶ ‹‹መገረፍህ፣ ስለ እኔ መገረፍ ይሁንልህ፣ የደምህ መፍሰስ ስለ እኔ ደም መፍሰስ ይሁንልህ፣ መቸንከርህም ስለ እኔ መቸንከር ይሁንልህ፣ ሞትህም ስለ እኔ ሞት ይሁንልህ›› ብሎ የሚከተለውን ቃልኪዳን ሰጥቷቸዋል፡- ‹‹ከዚህ ቦታ መጥቶ የተሳለመውን እምርልሃለሁ፤ ነፍሱ በአንተ ቃልኪዳን የማይማር በአንተ ቦታ ለመሳለምም፣ ንስሓ ለመግባትም ሆነ ለመቀበር አላቀርብብህም፤ መጥቶም የተቀበረውን ሥጋውን አፈር አይበላውም›› የሚል እጅግ ድንቅ ቃል ኪዳን ነው መድኃኔዓለም የሰጣቸው፡፡ ቃል ኪዳኑንም የሰጣቸው ቅዱሳን መልእክትን፣ ነቢያትን፣ ሐዋርያትን፣ ጻድቃንን፣ ሰማዕታትን፣ ቀሳውስትን፣ ዲያቆናትን፣ ደናግል መነኮሳትን ሁሉ ምስክር አቁሞ እንደሆነ ቅዱስ ገድላቸው ይናገራል፡፡ ይህም ድንቅ ቃልኪዳን ዛሬም በገሀድ እየታየ ነው፡፡ እስከ ዕለተ ምጽዓትም ሲታይ ይኖራል፡፡ በደጃቸው የተቀበረ ሰው አይበሰብስም፡፡ ይህም የሥጋው አለመበስበስ ለሞተው ሰው ለሥጋው አንዳች ረብ ጥቅም ኖሮት ሳይሆን የጻዲቁ ቃልኪዳናቸው እስከ ዕለተ ምፅዓት ድረስ ተፈጻሚ መሆኑንና ምልክትን ለሚሻ ለዚህ ክፉ ዘመን ትውልድ ምልክት ይሆን ዘንድ ነው፡፡
ከአ.አ 225 ኪ.ሜ ርቀት ለመራኛ ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው የሚዳ አቡነ መልከጼዴቅ ገዳም ተፈጥሮአዊ አቀማመጡ እጅግ አስገራሚ በሆነው ዋሻ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሁሉም ነገር በግልጽ ይታያል፡፡ ይህም እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ሁሉ በተለይም እኛ ኢትዮጵያውን በኃጢአት ሳንጠፋበት የመዳኛ መንገድ አድርጎ የሰጠን ድንቅ የቃል ኪዳን አባታችን መሆናቸውን ተረድቶና አውቆ በቃል ኪዳናቸው መጠቀም መቻል በራሱ ዕድለኛነት ነው፡፡ አቡነ መልከጼዴቅ ጌታችን ዕድሜአቸው ረጅም መሆኑን በምሳሌ እያሳየ ሲነግራቸው ‹‹በዚህ ዓለም መኖር ጥቅሙ ምንድር ነው? ወደ እረፍትህ ውሰደኝ እንጂ›› ብለው ሞታቸውን የለመኑ ቅዱስና ጻዲቅ አባት ናቸው፡፡
የአቡነ መልከጼዴቅ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን በጸሎታቸው ይማረን!

Photos 05/02/2017

ጌታችን 5 እንጀራ 2 ዓሣ አበርክቶ 5 የገበያ ሕዝብ እንደመገበ፡- በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመዘገበው ይህ የጌታችን ተአምር በውስጡ ብዙ ምሥጢራትን የያዘ ነው እንጂ ስለ ሥጋዊ ምግብ ብቻ የተነገረ አይደለም፡፡ ማቴ 14፡13-23፡፡ የተመገቡትና የተቆጠሩት አምስት ሺህ ወንዶች ብቻ ናቸው እንጂ ሴቶችና ሕጻናት አልተቆጠሩም፡፡ ይህስ ለምን ነው ቢሉ ሴቶች በአደባባይ ሲበሉ በሃፍረት ዳር ዳር ስለሚሉ ነው፡፡ ሕጻናት ደግሞ ከሚበሉት የሚፈረፍሩት ይበዛልና ነው፡፡
ጌታችን ያንን ሁሉ ሕዝብ በመንደር አጠገብ ሊመግባቸው ሲችል ለምን አርቆ ወደ ምድረ በዳ ወሰዳቸው ከተባለ ስለ ሁለት ምክንያት ነው፡፡ አንድም ‹‹ጥንት አባቶቻችሁን ከመንደር (ከግብጽ) አውጥቼ አርባ ዘመን ሙሉ መና የመገብኳቸው እኔ ነኝ፤ አሁንም በሥልጣኔ በተአምራቴ መገብኳችሁ›› ሲላቸው ነው፡፡ ሁለትም ጌታችን ተአምራቱን ከመንደር አጠገብ አድርጎት ቢሆን ኖሮ ሁልጊዜ ክፋትንና ጠማማ ነገርን ማሰብ ለአይሁድ ልማዳቸው ነውና ‹‹ፈጣን ፈጣን ደቀ መዛሙርቱን በጎን ወደ መንደር እየላከ ያስመጣው ነው›› ይሉት ነበር፡፡ ስለሆነም ጌታችን ለጥርጥር ምክንያት እንዳይኖራቸው አድርጎ ነው ተአምራቱን የገለጠላቸው፡፡ ጊዜውም አመሻሽ ላይ ነበርና ምሽት ላይ ያደረገበትም ምክንያት ጠዋት ላይ ቢሆን ኖሮ ‹‹የበላነው ሳይጎድል ነው ያበላን›› ብለው ከማመን ይርቁ ነበር፡፡
በተጨማሪም በበረሃ ያውም በምሽት ሕዝቡን በውኃ አጠገብ በሣር ላይ አስቀምጧቸው መመገቡ ‹‹በፍጻሜው ዘመን በምቹ ስፍራ በመንግሥተ ሰማያት መንፈሳዊ ምግብ እመግባችኋለሁ፤ በውኃ (በጥምቀት) በሚገኝ ክብርም አከብራችኋለሁ›› ሲላቸው ነው፡፡ ተአምራቱን ከውኃ ዳር ማድረጉ ‹‹መታጠቢያ ብናጣ በደንብ ሳንበላ ቀረን›› እንዳይሉ ነው፡፡ ሳር የበዛበት ቦታ ላይ ማድረጉም ‹‹መቀመጫ ብናጣ በደንብ ሳንበላ ቀረን›› እንዳይሉ ነው፡፡
አምስቱ እንጀራ የአምስቱ አዕማደ ምሥጢር ማለትም የምሥጢረ ሥላሴ፣ የምሥጢረ ሥጋዌ፣ የምሥጢረ ጥምቀት፣ የምሥጢረ ቁርባንና የምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ሁለቱ ዓሣ ደግሞ የፍቅረ እግዚአብሔርና የፍቅረ ቢጽ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ፍቅረ እግዚአብሔር ማለት እግዚአብሔር አምላክን በፍጹም ነፍስና በፍጹም ሐሳብ መውደድ ነው፡፡ ፍቅረ ቢጽ ደግሞ ባልንጀራን እንደራስ አድርጎ መውደድ ነው፡፡ አንድም ደግሞ እንጀራውና ዓሣው የቅዱስ ሥጋውና የክቡር ደሙ ምሳሌ ነው፡፡ አማኑኤል በቸርነቱ ይማረን!
50 minutes ago · Public · in Timeline Photos

Want your place of worship to be the top-listed Place Of Worship in Addis Ababa?
Click here to claim your Sponsored Listing.

Website

Address


Addis Ababa