Ethio-Lab Page

Ethio-Lab Page

Share

This page is created by members of Ethiopian Medical Laboratory Professionals to serve as an outlet for activities performed in the health facilities, research institutes, and universities.

15/02/2021

የኮሮና ክትባት ተስፋዎች፣ ስጋትና ፖለቲካ
==================

ምዕራባውያን 5 ሃያል የሆኑ የኮሮና መከላከያ ክትባቶችን ሰርተናል አሉ፡፡ የመከላከል አቅማቸውም ቫይዘር 95 %፣ ሞደርና 94.8 % እና አሰትራ ዜኒካ 70.4 % ወዘተ ነው አሉን፡፡

የአሰትራ ዜኒካን ክትባት በደቡብ አፍሪካ ለተነሳው አዲሱ ዝርያ መከላከያነቱ/ፈዋሽነቱ 10-25 % ብቻ ነው ተባለ፡፡ የጆንሰን ጆንሰንም፣ የኖቫቫክስም በአድሱ የደቡብ አፍሪካ ኮሮናቫይረስ ዝርያ(B.1.351 ወይም 501.V2),) ውጤታማነታችው አነስተኛ ናቸው፡፡ የጆንሰን ጆንሰን ክትባት ቀላል የህመም ምልክቶችን ለማስቀረት አቅሙ 57 % ሲሆን፤ ናቫቫክስ ደግሞ 49 % ነው፡፡

የአሰትራ ዜኒካን ክትባት ምርምርና ስርጭት የምትመራው ጊልበርት፣ እየቀባጠረች ነው፡፡አስትራ ዜኒካ በእንግሊዝ የተነሳውን አዲሱን ቫይረስ (B.1.1.7) ጨምሮ በጥሩ ብቃት እንደሚከላከል ቢገልፁም መረጃው ላይ በርካታ ብዝታዎች አሉ፡፡ የዚህ ክትባት በአዲሱ የእንግሊዝ ዝርያ ላይ ያሳየው ውጤታማነት 21.9% ብቻ ነው፡፡

የካቲት 21/2021 የአለም የጤና ድርጅት ባወጣው መረጃ መሰረት ሀገራት በትብብር ለመስራት እያሳዩት ያለው ዳተኝነትና የራሴን ዜጋ ብቻ የሚለው የበቀል አካሄዲ ወረርሽኙ ያሉትን ክትባቶች እንዲላመዳቸው ያደርጋል እንጅ መፍትሔ አይደለም እያሉ ነው፡፡ የራስህን ዜጋ ከትበህ ሌላውን መተው ከሞራል አንፃርም ትክክል አይደለም፡፡

በአንድ ጥናት መረጃ መሰረት ክትባት ያላቸው ሀገሮች የራሳቸውን ዜጋ ቢከትቡና ክትባት የሌላቸው ሀገራት ቤታቸውን በመዝጋት ከቤታቸው ቢቀመጡ፣ ሀብታም ሀገሮች እስከ 4.5 ትሪሊዮን ዶላር እንደሚከስሩ ያመለክታል፡፡

አሁን በክትባት እየታየ ያለው የእኔ ዜጎች ብቻ ይከተቡ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው አርቲፊሻል የእቃ አቅርቦት እጥረትና ዋጋ መናር ጋር ይመሳሰላል፡፡ ሀብታም ሀገራት ከራስ ፍላጎት በላይ ላለማምረት እያሳዩት ያለው ዳተኝነት፣ ተጨማሪ አዳዲስ ዝርያዎች እንዲፈጠሩ ከማድረግ ያለፈ ፋይዳና ትርፍ የለውም፡፡

እስከሁን ድረስ ከ30000 በላይ የጤና ባለሙያዎች በኮቪድ-19 ምክንያት ሞተዋል፡፡ አሁን ደግሞ ዘንዶው ኢቦላ ቫይረስ እንደተነሳ መረጃዎች እየወጡ ነው፡፡ የአደገኛ ጀርሞች ጭፈራና ፉከራና የአለም ዲንቀርና አስፈሪ ነው፡፡

13/01/2021

የአመቱ በጎ ሰው!!!
=========

ሟች ጎንደር አርማጭሆ ማሰሮ ደንጎር በምትባል የገጠር ቀበሌ ተወልዶ ያደገ ምስጉንና ቅን አገልጋይ ነበር፡፡ የሟች ጓደኛ ደግሞ ከጎጃም ክፍለ ሀገር ነው፡፡ ሁለቱም ቅንና ተግባቢ ስለነበሩ የሚተማመኑ ጓደኛሞች ለመሆን ጊዜ አልፈጀባቸውም፡፡ እናማ የሟች ሚስት ወልዳ ለመታረስ ጎንደር፣ የሟች የጓደኛ ባላቤት ደግሞ ለትምህርት ወደ ዩነቨርሲቲ ሲሄዱ፣ ሁለቱ ጊዜያዊ ላጤ ሆነው፣ አብረው ዉለዉ አብረው የሚያድሩ ጓደኛሞች ሆኑ፡፡ ሟች ከጨጓራ ጋር ተያይዞ ያመዉ ስለነበር ህመሙ እየጠናበት ሲመጣ፣ ወደ ጎንደር በማቅናት ከባለቤቱና ልጆቹ ጋር በመሆን እረፍት በመውሰድ እራሱን ዘና እያደረገ በሽታውን ለመቆጣጠር ቢሞክርም ሊሻለው አልቻለምና ጎንደር ሆስፒታል፣ ከዚያም ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተንከራተተ፡፡ ከ6 ዙር በላይ ኬሞ-ቴራፒ ወሰደ ሊሻለው አልቻለምና የስልክ ግንኙነታቸው ቷቀረጠ፡፡

አንዷ ቅንና ባለራዕይ የስራ ባልደረባችን የደረሰ ጉዳይ እያሳሰበኝ ነዉ እባካችሁ ቶሎ ሄደን አይኑን እንየው ስትል የሰማዉ ይህ ቅን ጓደኛዉ ባለቤቱንና ጓደኞቹን በመያዝ የመጨረሻዋ ቀን ጎንደር ይገባል፡፡ ይች ቀን ለካም ወንድማችን ደረሰ የመጨረሻዋ ቀን ነበረችና ከቤቱ ስንደርስ አይደለም ሰው መለየት ቀርቶ በግዴታ ጠጣ እየተባለ የሚጋተውን የባህል መድሃኒት እንኳ መከላከል አቅቶት፣ ተውኝ እያለ እያለቀሰ አገኘነው፡፡የሚያውቀው ሰውነት ፈርሶ ከፍራሹ ጋር ተጣብቆ ሲያየው የዚህ ቅን ወንድም እምባ ሊቆም አልቻለም፡፡ ተስፋ በመቁረጥ ከእንግዲህ ከእሱ ጋር ሳይሆን ያስረከበኝ የልጆቹ ጉዳይ ያሳስበኛል በማለት በሀሳብ ውስጥ ሆኖ ባህር ዳር እንደገባን አርፏል የሚል መርዶ ሰማን፡፡ ሳይነጋ ተመልሶ በመሄድ አፈር አልብሶ፣ የልጆቹንና የባለቤቱን እምባ አብሶ ተመለሰ፡፡

መልካምን ነገር ወደ ተግባር መቀየር ባህሪው የሆነው ይህ ቅን ጓደኛ ከጓደኞቹ የሰማቸውንና የራሱንና የባለቤቱን ሀሳብ ጨምሮበት፣ አካውንት በመክፈት ጓደኛየን ያጣሁ ወንድማችሁ ነኝ፡፡ እኔን የምትወዱኝ ከሆነ፣ የደረሰ ልጆችም የሚያሳዝኗቹህ ከሆነ ዛሬ እርዱኝ በማለት በፌስቡክና ቴሌገራም በመክፈት ተሯሯጠ፡፡ የበርካታ ቢሮዎችን ደች አንኳኳ፣ ከበርካታ ተሰብሳቢዎች ፊት ቆሞ አቤት አለ፡፡ ቅን የስራ ሰው ስለነበር አይደለም በሚሰራበት አማራ ክልል በመላ ኢትዮጵያ የእሱን ስም የማያወቅ የላቦራቶሪ ባለሙያ የለም፡፡ በአማራ ክልል ከተራ የጤና ጣቢያ ሰራተኛ እስከ ክልል ምክር ቤት በአካል ባያውቁት እንኳ በስም ይታወቃል፡፡ ስለሆነም ጠይቆ አላፈረም፤ ካሰበው በላይ ተሳክቶለት ገንዘብ በማሰባሰብ የወደቁትን የጓደኛውን ቤተሰቦች መሰብሰብ ችሏል፡፡ መልካምነትን ወደ ሀብት በመመንዘር ከኪራይ ቤት አውጥቶ መጠለያ ገዝቶ አስገብቷቸዋል፡፡

የኢትዮ-ላብ ፔጅ አስተዳዳሪዎች ይህን ሰው የአመቱ በጎ ሰው ብለው እውቅና የሰጡት ሲሆን እውቅናውን ያገኘበት ምክንያት ደግሞ በሟቹ ጓደኛው ልጆች ስም እርዳታ በማሰባሰብ ኮንዶምንየም ገዝቶ በመስጠት ስላደረገው የላቀ ማህበራዊ ስራው ነው፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ በኢትዮጵያ የህብረሰተሰብ ጤና አጠባበቅ ማህበርና የኢትዮጵያ የህክምና ላቦራቶሪ ማህበር የአመቱ በጎ ሰው ብለው ቢሸልሙት ያንስበት ይሆናል እንጅ አይበዛበትም፡፡ ስለሆነም ይህን ጥቆማ አየሰጠን ስናስተዋውቃችሁ በታላቅ ደስታ ነው፡፡ ይህ ሰው ሙላቱ መለሰ ይባላል ከአማራ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲት!! ከጎኑ ሆና በሀሳብ የምትደግፈው ባለቤቱ ደግሞ ማህሌት ወርቁ ትባላለች፡፡

ወንድማችን ሙላትና እህታችን ማህሌት እንኳን ያሰባችሁት ተሳካ!! ከደግ ሰው ጋር መዋል ምንኛ የህሊና እረፍትን ይሰጣል!!!፡፡ እኛም ከአንተ ብዙ መልካም ነገሮችን ተምረናልና እናመሰግናለን!!!

11/01/2021

የኢትዮጵያ ላቦራቶሪ ባለሞያውች ሚና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምላሽ
==================

በዓለም አቀፍ ደረጃ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ ደረጃ ሀገራችን በማገልገል ላይ ያሉ የኢትዮጵያ የላቦራቶሪ ባለሞያዎች ሚና ላቅ ያለ ነበረ፡፡

ባለሞያዎቹ ነባር የመንግስትና የግል ከዚህ ቀደም ለሌሎች በሽታዎች (ኤች አይ ቪ፣ ሳንባ ነቀርሳ፣ ወባና የመሳሰሉት) የምርመራ አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ የሞሎኩላር ላቦራቶሪዎችን ለኮቪድ-19 ምርመራ በአዲስ መልኩ አደራጅተዋል፡፡ በተጨማሪም አዳዲስ የሞሎኩላር ላቦራቶሮችን ለኮቪድ-19 ምርመራ አመቺ ሆነው በአጭር ጊዜ ውስጥ ተሰርተው፣ የሚጠበቅባቸውን የቅድመ ምርመራ ልኬት አቅም ግምገማ በተሳካ ሁኔታ አልፈው የምርመራ አገልግሎት እንዲሰጡ ከፍተኛ አስተወፆ አድርገዋል፡፡ በዚህም በአሁኑ ሰዓት 73 ላቦራቶሪዎች በሀገራችን የኮቪድ-19 ሞሎኩላር ምርመራ በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ 16ቱ የግል ተቋማት ናቸው፡፡ በእነዚህም ሞሎኩላር ላቦራቶሪዎች ከ1.8 ሚሊዮን ባላይ ግለሰቦች የሞሎኩላር የኮቪድ-19 ምርመራ ተደርጎላቸዋል፡፡ አገልግሎታቸውንም ቀጥለዋል፡፡

በዚህም እስከ ታህሳስ 29 ቀን 2013 ዓ.ም ድርስ 127, 227 በኮቪድ-19 የተጠቁ ግለሰቦችን መለየት ተችሏል፡፡ ይህም ከተያዙት ግለሰቦች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የነበራቸውን ሰዎች እራሳቸውን ለተወሰነ ጊዜ በማግለል የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት በከፍተኛ ሁኔታ አግዟል፡፡ በተለይ ክትባት በሌለበት ጊዜና ክትባቱ ወደ ሀገረችን ባልገባበት ሁኔታ የላቦራቶሪ ምርመራ ለበሽታው ቁጥጥር ሚናው ከክትባት አይተናነስም፡፡

የኢትዮጵያ ላቦራቶሪ ባለሞያዎች 1, 836, 527 ምርመራዎችን ለማከናወን ከምርመራው ውስብስብነት፣ ውጤት ለማድረስ ከሚወስደው ጊዜ እና በሀገራችን የሞሎኩላር ላቦራቶሪዎች ቁጥር ውስንነት ምክንያት ከመንግስት የሥራ ሰዓት ውጭ (አዳርና በዓላትን ጨምሮ) ከቤተሰባቸው እራሳቸውን በማግለል ማህበረሰባቸውን በማገልገል ሀገራዊ ግዴታቸውን ተወጥተዋል፣ በመወጣት ላይም ይገኛሉ፡፡

ለዚህም አገልግሎታቸው ከአንዳንድ ሚዲያዎች የላቦራቶሪ ባለሞያዎች ምስጋናን ተችሯቸዋል፡፡ ለምሳሌ ሸገር 102.1 በተደጋጋሚ አየር ላይ ምስጋና ሲያስተላልፍ አድምጨዋለሁ፡፡ ምንም እንኳን ጣቢያው ባለሞያዎቹን የገለፀበት መንገድ ውስንነት ቢታይበትም፤ የ "ላቦራቶሪ ቴክኒሻኖች" በማለት ቢሆንም፡፡

የላቦራቶሪ ሞያ በኢትዮጵያ በመጀመሪያ (BSc)፣ በሁለተኛ (MSc)ና በሶስተኛ (PhD) ድግሪዎች አልፎም በሙሉ ፕሮፌሰርነት ደረጃ በሚገባ ቢገኝም የማህበረሰባችንና ማህበረሰብን ማንቃት የሚጠበቅባቸው ሚዲያዎቻችን አረዳድ ውስንነት በግልፅ የሚታይ ነው፡፡

የ "ላቦራቶሪ ቴክኒሻን" በዲፕሎማ የትምህርት ደረጃ የሚገኙ የላቦራቶሪ ባለሞያዎች ብቻ የሚገልፅ ስያሜ መሆኑን ያለመረዳት ይታያል፡፡ ነገር ግን በሀገራች የኮቪድ-19 ምርመራን በማሳለጥ ሚናቸውን የተወጡ የላቦራቶሪ ባለሞያዎች ደረጃ ግን ከላይ አንደገለፅኩት በተለያዩ የትምህርት ደረጃዎችና ስፔሻሊቲዎች የሚገኙትንም ያካትታል፡፡

ሆኖም በሸገር 102.1 በተደጋጋሚ ሲደረግልን የነበረውን ምስጋና ሙሉ በሙሉ ከልብ ተቀብለናል፡፡ እናመሰግናለን!

አበባው ከበደ (ከኢ.ህ.ጤ.ኢ)

SHEGER FM 102.1 RADIO
Lia Tadesse, Minister of Health

Want your practice to be the top-listed Clinic in Addis Ababa?
Click here to claim your Sponsored Listing.

Category

Website

Address

Addis Ababa